ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ለ170 ህፃናት የነርቭ ህክምና መስጠቱን አስታወቀ

103
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ከመጋቢት 10 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለህክምናው ወረፋ ከሚጠባበቁ 771 ህጻናት ከ170 ለሚልቁት የነርቭ ህክምና በዘመቻ መስጠቱን ገለጸ። በላቦራቶሪ ረገድ ያለበት ችግር የታሰበውን ያህል እንዳይንቀሳቀስ እክል እንደፈጠረበትም ገልጿል። ሆስፒታሉ የታካሚዎች ቁጥር ከፍ እያለ በመምጣቱ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የዘመቻ ስራውን እንደጀመረ ነው የተገለፀው። በሆስፒታሉ የአንጎልና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ታደሰ ከበደ ለኢዜአ እንደገለፁት በሆስፒታሉ ህክምና ለማግኘት ለረጅም ጊዜ እየጠበቁ ያሉ 771 ህፃናት በመኖራቸው ምክንያት ነው ወደ ዘመቻ ስራ የተገባው። ዘመቻው ከተመጀረ ወዲህ በሆስፒታሉ ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉ 22 ቀናት ቀዶ ህክምና በማድረግ 110 ህፃናትን ማከም እንደተቻለ ተናግረው፤ ከጥቁር አንበሳ በሚመጡ ሐኪሞች ህክምና ያገኙ ህፃናትን ጨምሮ የታካሚዎቹ ቁጥር ከ170 በላይ ደርሷል ብለዋል። ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት በሳምንት አንድ ቀን ቀዶ ህክምና ይሰጥ እንደነበርና በሳምንት እስከ 15 ህፃናት ህክምና ያገኙ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ግን በየቀኑ አምስት ቀዶ ህክምና እንደሚደረግ ነው ያብራሩት። ባለፈው ሳምንት ከሐሙስ እለት ጀምሮ የላብራቶሪው መበላሸት ህክምናውን እንዳያከናውኑ ማድረጉን ገልፀው ፤ ችግሩን ለሆስፒታሉ አስተዳደር መናገራቸውን አስረድተዋል። በሌላ በኩል አገልግሎቱን ለማግኘት የሚመጡ ሰዎች አሁንም ወረፋው እንዳስመረራቸው ይናገራሉ። አቶ ታደለ መኮንን ልጃቸው ስትወለድ ጀምሮ አንገቷ ላይ የነበረባትን እባጭ ለማሳከም ከአርሲ ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ሳምንት እንደሞላቸው ይገልፃሉ። ከዓመት በፊት የጠበቁት ወረፋ ደርሶ ልጃቸውን ይዘው ለህክምና ቢመጡም አገልግሎቱን አግኝተው ወደቤታቸው አልተመለሱም። ወይዘሮ መሰረት ያደታም ከቡራዩ ወደ ሆስፒታሉ ያቀኑት ልጃቸው ስትወለድ ጀምሮ በወገቧ ላይ ያለባትን እባጭ ለማሳከም ነው። ከሁለት ዓመት በላይ ጠብቀው ቀጠሮ አግኝተው ሆስፒታሉ መጥተውም ልጃቸው ህክምና አላገኘችም። ከሐሙስ ማታ ጀምሮ ህንፃው ላይ ከሚገኙ ሻወር ቤቶችና መፀዳጃ ቤቶች የመጣ ፍሳሽም ላብራቶሪው ውስጥ በመፍሰሱ ከድንገተኛ ውጪ የላብራቶሪ አገልግሎት መቋረጡን የሚገልፁት ደግሞ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር የኔአለም አየለ ናቸው። ህንፃው የቆየ ስለሆነ ፍሳሹ ሊከሰት መቻሉንና ለእድሳት እየተጠና መሆኑን ገልፀው ሆስፒታሉ በጊዜያዊነት ከዓርብ እስከ እሁድ እድሳት በማድረግ ከሰኞ ጀምሮ ላብራቶሪው አገልግሎት እንደጀመረ ተናግረዋል። ዘመቻው በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከምኒሊክ ሆስፒታል ጋር በመሆን ህክምናው ምኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ ባለ ትርፍ አልጋ በተጨማሪ እንደሚከናወንም ገልፀዋል። ሆስፒታሉ በምኒሊክ ሆስፒታል ለሚከናወነው ቀዶ ህክምና የሚያገለግሉ ግብዓቶችን እንዳዘጋጀ ገልፀው ባለሙያዎችም የነርቭ ሐኪም ካለባቸው ሆስፒታሎች መጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ እንደታቀደ አብራርተዋል። በእርግዝና ወቅት በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የህፃናት አንጎልና ህብለ ሰረሰር መጎዳት ነፍሰ ጡር እናቶች ፎሊክ አሲድ በበቂ መጠን ካላገኙ የሚከሰት ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ህፃናቱ በጀርባቸውና አንገታቸው ላይ እብጠት ይወጣና ጭንቅላታቸው ትልቅ ይሆናል። በሽታውን ለመከላከል ማንኛውም በመውለድ እድሜ ላይ ያለች ሴት ከማርገዟ በፊትና ካረገዘች በኃላ ባሉት የመጀመሪያ ወራት ፎሊክ አሲድ የተባለውን እንክብል መውሰድና በፎሌት የበለፀጉ እንደ ምስር፣ ሽንብራ አቮካዶና አረንጓዴ ቅጠሎችን በመመገብ መከላከል እንደሚቻል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም