በትግራይ በድህረ ኮሮና የቱሪዝም ፍሰቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ የቅርሶች ጥገና እየተካሔደ ነው

53

መቐለ (ኢዜአ) ሓምሌ 25/2012ዓ/ም  በትግራይ በድህረ ኮሮና የቱሪዝም ፍሰቱን ወደነበረበት እንዲመለስና የበለጠ እንዲጠናከር በማሰብ ጥገና እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለፀ ። 

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግኑኝነት  ባለሙያ አቶ አባዲ ደስታ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ ጥንታዊ  ቅርሶች ህልውናቸውን በመጠበቅ  ለጎብኚዎቹ ምቹ ለማድረግ የጥገና ስራ እየተከናወነ ነው ።

 በ11 ሚሊዮን ብር ወጪ ጥገና እየተከናወነላቸው የሚገኙ ቅርሶች ከ4ኛው እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን የተገነቡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና ቤተ መንግስት ይገኙበታል ።

በኢሮብ ወረዳ የሚገኝና በአራተኛ ክፍለ ዘመን የተገነባው  የማርያም ጉንዳጉንዶ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን  በእድሜ ብዛት በማርጀቱ ጣሪያውን የመጠገን ስራ እየተካሄደ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል።

በኽልተ አውላዕሎ ወረዳ የሚገኝና  ከአለት የተፈለፈለ  ጥንታዊ  የአቡነ አብርሃ ደብረፅዮን ውቅር ቤተክርስትያንም የውስጥ ጥገናና አጥር እንዲሰራለት ተደርጓል ።

በ14ኛው ክፍለ ዘመን  በውቅሮ ከተማ  የተገነባው    ጨርቆስ  ውቅር ቤተክርስትያንና በጉሎመኸዳ ወረዳ የሚገኝ የአቡነ ተክለሃይማኖት ፃራዕሮ  ጥንታዊ ቤተክርስትያን ጥገና ከተደረገላቸው ቅርሶች መካከል ይጠቀሳሉ ።

በአጉላዕ ወረዳ የሚገኘው የአፄ ዮውሃንስ አራተኛ ቤተመንግስት ባህላዊ ቤተመዘክር ሆኖ እንዲያገለግል ታስቦ ጥገና የተደረገለት መሆኑንም አቶ አባዲ ተናግረዋል ።

 የቅርሶቹ ጥገና ጥንታዊነታቸውና ውብ ስነ ጥበባዋ ይዘታቸው ሳይለቅ በጥንቃቄ እየተጠገኑ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በቢሮው የስነ ህንጻ እቀባ ባለሙያ አቶ መኮነን ሓጎስ ናቸው።

በቅርስ ጥገና ስራው የአካባቢው ህብረተሰብ በጉልበቱና ቁሳቁስ በማቅረብ የተሳተፉ መሆናቸውን  የገለጹት ባለሙያው ይህም ማህበረሰቡ ለቅርስ ጥበቃ ያለው ተነሳሽነት ያመለክታል ብለዋል።

የውቅሮ ጨርቆስ ቤተክርስትያን አገልጋይ ቄስ መልአከ ጸሀይ አብረሀ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኑ በእድሜ ብዛት ምክንያት  በተወሰነ የግንቡ ክፍልና ጣሪያው ላይ ውሃ እየገባበት የመበስበስ ምልክት አሳይቶ ነበር ብለዋል ።

አሁን ግን መንግስት በመደበው በጀት ተጠግኖ የቀድሞ መልኩ መያዙን አስረድተዋል።

በአጉላዕ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ የአጼ ዮሀንስ አራተኛ ቤተመንግስቱ ለዓመታት እድሳት ሳይደረግለት በመቆየቱ ግንቡ አርጅቶ ለአደጋ ተጋልጦ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የአጉላእ ከተማ ነዋሪ አቶ ክንፈ ወርቀልኡል ናቸው።

አሁን ቤተመንግስቱ እድሳትና አጥር ተሰርቶለት የድሮ ውበቱ መመለሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም