በመዲናዋ በአንድ ጀምበር ለሚተከለው 2 ሚሊዮን ችግኝ ህብረተሰቡ አረንጓዴ አሻራውን እንዲያስቀምጥ ጥሪ ቀረበ

71

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በአንድ ጀምበር ለሚተከለው 2 ሚሊዮን ችግኝ  ህብረተሰቡ አረንጓዴ አሻራውን አንዲያስቀምጥ የከተማዋ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቀረቡ ።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ መርሃ ግብሩን አስመልክተው ከከተማዋ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተው መግለጫ ሰጥተዋል።

ዘንድሮ በአዲስ አበባ  ለመትከል ከታቀደው 7 ሚሊዮን ችግኝ እስካሁን አንድ ሚሊዮን ሰዎች  4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አውስተዋል።

በነገው እለትም  በመዲናዋ በአንድ ጀምበር 2 ሚሊዮን ችግኞች  እንደሚተከሉም ገልጸዋል።

የእንጦጦ ልማት ያለፈው ትውልድ አረንጓዴ አሻራ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው አዲስ አበባን ለቀጣዩ ትውልድ ጎርፍ የማይፈራረቅባትና ፀሃይ የማያቃጥላት ከተማን ማቆየት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የነዋሪዎቿ የጋራ ቤት የሆነችውን አዲስ አበባን ለመገንባት የመኖሪያ ቤት ጓሮን ጨምሮ ሁሉም በያለበት አረንጓዴ አሻራውን እንዲያሳርፍም ጠይቀዋል።

በተለይ ለከተማ ግብርናና ለምግብነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀው፤ የችግኝ ተከላው መርሃ ግብር ነገ ማለዳ 12፡00 ሠዓት ጀምሮ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ችግኝ ተከላው ለኮቪድ-19 በማያጋልጥ መልኩ አካላዊ ርቀትና ንጽህናን በመጠበቅ እንዲሁም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን በመጠቀም እንዲከወንም አሳስበዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ለመተባባር ስራ በማሳያነት በመጥቀስም ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የስፖርት ቤተሰቦች የጋራ ለሆነችው ከተማ ግንባታ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም