በምእራብ ጎንደር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የአቅመ ደካሞች የእርሻ መሬት በዘር እንዲሸፈን አደረጉ

51

መተማ (ኢዜአ) ሐምሌ 25 /2012 ''በምእራብ ጎንደር ዞን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ጦም ለማደር ተቃርቦ የነበረ የእርሻ መሬታቸው በዘር እንዲሸፈን እንዳደረጉላቸው አቅመ ደካማ አረጋውያንና ሴቶች ገለፁ ፡፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን 82 ሺህ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ማህበረሰቡን በማገልገል ላይ ይገኛሉ ተብሏል ።

በመተማ ወረዳ ኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እናትነሽ ሙላቱ ለኢዜአ እንደገለፁት ''በአቅም ማነስ ምክንያት የእርሻ መሬቴ በሰብል ሳይሸፈን ይቀራል የሚል ስጋት ገብቶኝ ቆይቷል'' ብለዋል።

‹‹ለስራ ያልደረሱና አባታቸውን በሞት የተነጠቁ ሶስት ህፃናት ልጆች አሉኝ፤ ለልጆቼም ሆነ ለእኔ ችግሬን ተረድቶ የሚረዳኝ ዘመድ የሌለኝ በመሆኑ ጭንቀት ውስጥ ገብቼ ነበረ'' በማለት ተደቅኖባቸው የነበረውን ስጋት ያስታውሳሉ ።

ሆኖም ግን ከዘመድ በላይ የሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አንድ ሄክታር መሬታቸውን በማሽላ ሰብል በመሸፈን ተስፋቸውን እንዳለመለሙት ገልፀዋል።

በወረዳው የመንደር 6 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ የዛብነሽ ዘለቀ በበኩላቸው በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ግማሽ ሄክታር መሬታቸው በዘር እንደተሸፈነና ቀደም ብሎ በሌላ ዘመድ የተዘራላቸውን ግማሽ ሄክታር የሰሊጥ ማሳም እንዳረሙላቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ወጣቶቹ በየአመቱ ይደግፉኛል›› ያሉት ነዋሪዋ ባለፈው አመት በወጣቶች በተሸፈነላቸው ግማሽ ሄክታር መሬትም ከ8 ኩንታል በላይ የማሽላ ምርት እንዳገኙ አስታውሰዋል፡፡

በቋራ ወረዳ ሰልፈረዲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሹሜ ደርሶ እንዳሉት ደግሞ የቀበሌው በጎ አድራጊ ወጣቶች የመኖሪያ ቤታቸውን ከመጠገን ባለፈ ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በማሽላ ሰብል እንደሸፈኑላቸው ተናግረዋል፡፡

በቀበሌው ለ20 ዓመታት መኖራቸውን ገልፀው ልጅ ባይኖረኝም የለኝም የአካባቢውን ወጣቶች እድሜና ጤና ይስጥልኝ እንጂ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉልኝ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ብለዋል ።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል በመተማ ወረዳ የኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሳሙኤል ይርጋ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሲሆን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፍ ትልቅ የህሊና እርካታ እንደሚሰጠው ተናግሯል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የትምህርት ቤቶችን አጥርና ወንበር መጠገን፣ የጤና አጠባበቅ ግንዛቤ መስጠትና የአረጋውያንንና ሴቶችን ማሳ በዘር የመሸፈንና የአረም ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል ።

በዞኑ የማህበራዊ ጉዳዮች ልማት መምሪያ የወጣቶች ጉዳይ አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ተገኘ እንደገለፁት በዘነድሮው  የክረምት ወቅት 82 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ ናቸው ።

ወጣቶቹ እስከ አሁን ባደረጉት እንቅስቃሴም 120 ሄክታር የአቅመ ደካሞችን መሬት በሰብል የመሸፈንና የአረም ስራ ማከናወናቸውን ፣ 90 ሺህ ችግኝ መትከላቸውንና መሰል ማህበራዊ አገልግሎቶች መስጠታቸውን ገልፀዋል።

ከሐምሌ 2012 ዓ/ም መግቢያ ጀምሮ ወጣቶቹ ባከናወኑት የበጎ ፈቃድ ልማት ስራም ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የጉልበት አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ  ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የመገመት ነፃ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከአስተባባሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም