''ትናንት ዛሬ አይደለም''

126

ከሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ)

ድምፃዊ ሙሉቀን መለሰ ዝናን ካተረፈባቸው ዘፈኖቹ አንዱ ''ትናንት ዛሬ አይደለም'' የሚል ርዕስ አለው።

''ወደኋላ ሄደሽ

በሐሳብ ከማለም

ቀን እንዳይመሽብሽ

ትናንት ዛሬ አይደለም''

እያለ ፍቅረኛ ስታማርጥ ወይም ጊዜ አለኝ ብላ ጊዜዋን በከንቱ ለምታሳልፈው ወዳጁ ጊዜሽን ተጠቀሚበት ይላል።

በዓባይ ወንዝ ጉዳይ የሚደራደሩት ሦስቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ኢትዮጵያ፤ሱዳንና ግብዕ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ሲደራደሩ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥረዋል።ሆኖም አንዳንዴ መግደርደር ሌላም ጊዜ ላስገድድ በሚል መንፈስ ይመስላል ዛሬም አልተቋረጠም።

እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ባላት የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ግብፅና ሱዳን ''ቀኑ መሽቶባችኋል'' የምትል አይደለችም።ከዓባይ ውሃ ኤሌክትሪክ አመንጭታ ውሃውን ለሁለቱ አገሮች ከማሳለፍ ያለፈ ፍላጎት የላትም።

ነገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌከትሪክ ፍላጎት አለመሟላቱ ራሱ መመለስ ያለበት ትልቁ ጥያቄ መሆኑን

ከማንሳት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው።

በኢትዮጵያ እያደገ ያለው ኢኮኖሚ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት በተለይም ወደ አገሪቱ እየገባ ያለው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨሰትመንት የኃይል አቅርቦትን ማሟላት ከመመለስ አኳያ ማየትም ይገባል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአየር ፀባይ ለውጥ ኢንስቲትዩት ተመራማሪው ኬቨን ዊለር ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት  ግብጻውያን ''የውሃ እጥረት ያጋጥመናል'' የሚለው ፍራቻ በዚህ ደረጃ ላይ መነሳት የለበትም። 

በሚቀጥሉት ዓመታት ድርቅ የሚከሰት ከሆነም፤ ችግሩ ያኔ ሊታይ ይችላል ይላሉ።

ነገር ግን በግብፅ የሚነሳው አታካራ በአካባቢው የመጣውን የወንዙን ተጠቃሚነት ፍላጎት ማደግ ያሳያል ይላሉ።

ሱዳንን በመወከል በግድቡ ድርድር የተሳተፉት ሂሻም ካሂን የግድቡ 80 በመቶ ክርክር ስምምነቱ አሳሪ መሆን አለበት የሚል ይዘት መያዙን አረጋግጠዋል።

ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው መንግሥት አስታውቋል።

ግንባታው ማከራከሩን ቢቀጥልም የህዳሴ ግድብ ወደ ሱዳን በሰከንድ የሚፈሰውን 19 ሺ 370 ኪዩቢክ ሜትር ጎርፍን አስቀርቷል ይላሉ።

በተጨማሪ ወደ ሱዳን የሚገባውን 100 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ደለል አፈር የሚያስቀርና 500 ሺህ ሄክታር አዲስ ለም መሬት ለግብርናው እንደሚያስገኝ ይናገራሉ።

ግድቡ ሲጠናቀቅ በሱዳን 40 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ቦታ ላይ የሚያጋጥመውን የጎርፍ አደጋ ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀርም አመልክተዋል።

ተመጥኖ የሚለቀቀው የግድቡ ውሃ በሱዳን ያለውን የግብርና ሥራ በማሳደግ የውሃ ትነትን በ''ከፍተኛ መጠን'' መቀነሱን አስረድተዋል።

በአስዋንና በሌሎች ግድቦች በትነት የሚባክነው የናይል ውሃ 19 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይጠጋል።

ግድቡ ደግሞ ከሌሎች ግድቦች አንፃር ትነትን በማስቀረት 6 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃን ከትነት ይታደጋል ይላሉ ምሁራኑ።

የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሓፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ “ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በመጠቀም ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ ትብብር የማይተካ ሚና” አለው ብለዋል።

“የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ መጠን የሚያሳድግ፣የኤሌክትሪክ ኃይል (መብራት)ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላታል "ብለዋል።

ወደ ኋላም ሳንሄድ፤ካለንበትም ሳንቆም፤በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሳንጎዳና ሳንጎዳ ተፈጥሮ ያዛመደንን፣መልክዓ ምድር ያስተሳሰረንን ከአንድ ወንዝ እየጠጣ የኖርን ሕዝቦች እንኳን ዛሬም ነገም  የሚያኖረን ሀብት እየተጠቀምን አብረን እንኖራለን።የዛሬውን እውነታ ተቀብለን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም