ለአረፋ በዓል እንኳን አደረሳችሁ --የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ

123

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለ1441ኛው ዓመት ሂጅራ የዒድል አዱሀ-አረፋ በዓል መልካም መግለጫ መልዕክት አስተላለፈ።

ሃይማኖታዊ ሽፋን ካደረገ ግጭት ራሱን እንዲጠብቅ አሰስቧል።

ጉባዔው በዓሉን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ለበዓሉ በሰላምና በጤና እንዲያሳልፈው መልካም ምኞቱን ገልጿል።

የዘንድሮው በዓል የሙስሊሞች ሁሉ ብቸኛ ተወካይ ተቋም የሆነው መጅሊስ በዓዋጅ እውቅና ባገኘበት ማግስትና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት መስጅዶች ዝግ በሆኑበት የጀመአ ስብስቦች ባልተፈቀደበት እንዲሁም የዒድ ሶላት በተለመደው ሁኔታ በማይሰገድበት ጊዜ የሚከበር በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አመልክቷል።

በኮቪድ 19 ምክንያትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የሐጅን ሥነ-ሥርዓት ማከናወን ያለመቻላቸው ክስተት ደግሞ ዓለም አቀፍ መገለጫው እንደሆነም ገልጿል።

ጉባኤው ከመሰረቱት ተቋማት አንዱና ዋነኛው የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤትና በሥሩ የሚገኙት መዋቅሮቹ እንደሆኑ ያስታወሰው መግለጫው፤በመንፈሳዊም ይሁን በልማታዊ አደረጃጀቱ  የተጠናከረ ተቋም መሆኑ አስፈላጊ እንደሆነና ከሌሎች የሃይማኖት ተከታይ ጋር በመተባበር የሰላም፣የመከባበርና የአብሮነት እሴቶችን እንደሚያጠናክር ተገልጿል።

ሕዝበ ሙስሊሙ አገሪቱ አሁን የምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ሃይማኖታዊ ሽፋን ያደረገ ግጭት ለመፍጠር የሚደረገው ሙከራ ሁሉ በሃይማኖት አስተምህሮ መሰረት የሌለውና የሚወገዝ፤ ከኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን ጋር የሚቃረን ተግባር መሆኑን በማጤን የአገሪቱ ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት እንዲጠብቁ ጉባኤው አሳስቧል።

በተጨማሪም ታላቁ የህዳሴ ገድብ የመጀመሪያ የሙሌት ሥራውን በስኬት እንዳጠናቀቀው ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለስኬቱ  እንዲተጉ  አስገንዝቧል።

የኮሮና ወረርሽኝ እየተባባሰ በመምጣቱ ሙስሊሙ በበዓሉ ወቅት ከጥንቃቄው እንዳይዘናጋ ያሳሰበው ጉባኤው፤ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር አስተምህሮቱ በሚያዘው መሰረት በኮሮናና ተያያዥ ችግሮች የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ያለውን በማካፈል እንዲያከብረው ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም