አርሶ አደሮች በአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሀ ግብር ለቡናና ለፍራፍሬ ልማት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው

55

ዲላ፣ ሐምሌ 24/2012 (ኢዜአ) የጌዴኦ ዞን አርሶ አደሮች በአረንጓዴው አሻራ የልማት መርሀ ግብር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የቡናና የፍራፍሬ ችግኞች በመትከል ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን ገለፁ ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል አርሶ አደር ንጉሴ አዱላ እንደገለፁት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች ለመትከል በአረንጓዴው አሻራ የልማት መርሀ ግብር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ።

ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 500 የቡና ችግኝ ፣ 150 የእንሰትና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች መትከላቸውን ገልፀዋል ።

ማንጎና አቦካዶ በስፋት በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸውን ችግኞች በሚፈልጉት መጠን ማግኘት ከቻሉ ተከላውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ።

አርሶ አደር ደበበ ጅሶ በበኩላቸው ቡናና ፍራፍሬ ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልፀዋል ።

ለቡና ማሳቸው የአፈር ለምነትን የሚጨምሩና ለጥላ የሚሆኑ ብርብራ ፣ ዋንዛ ፣ ዋርካና መሰል ሀገር በቀል ዛፎችን ከመትከል ባለፈ በአጭር ጊዜ ለገበያ የሚበቁ የተሻሻሉ የአቡካዶ፣ የፓፓያና ማንጎ ችግኞችን ተክለው እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በተያዘው አመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ30 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን የሚናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ናቸው።

ከተተከሉት ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ጽድ፣ ዋንዛ፣ ብሳናና መሰል ሀገር በቀል ዛፎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ እቅድን ከማሳካት ባለፈ በዲላ ከተማ በግንባታ ላይ ለሚገኘው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪያል ፓርክ ግብዓት የሚሆኑ የፍራፍሬ ዝርያዎች መተከላቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ ከ40 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የአቦካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያና አፕል የችግኝ ዝርያዎችን በግዥ ቀርቦ አርሶ አደሩ በጓሮው እንዲተክል መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ በዞኑ ወናጎና ዲላ ዙሪያ ወረዳዎች በ3 ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ችግኝ ማፍያ ጣቢያ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን አስረድተዋል።

የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በበኩላቸው በክልሉ ከአረንጓዴ አሻራ የማኖር ስነስርዓት ጎን ለጎን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፍራፍሬ ችግኞችን የማልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይ የመሬት ጥበት ባለባቸው ዞኖች ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የፍራፍሬ ዝርያዎች በስፋት በመተከል ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል ።

ችግኞችን ተንከባክቦ ለማሳደግ የቅርብ ክትትል የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው፣የማይጸድቁትን ለመተካት መጠባበቂያ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም