ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ልማትና ሰላም አስተዋጽኦውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

104

ድሬዳዋ ሐምሌ 24/2012(ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላምና ልማት መረጋገጥ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል  ተጠየቀ። 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ  1ሺህ 441ኛውን የኢድ አል አድሀ/አረፋ/ በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላይ እንደተናገሩት ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳት ሊያከብረው ይገባል፡፡

የመታዘዝ ታላቅ ጸጋ የሚገለጥበት በዓል በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው ነዋሪ   ራሱን ከኮሮና በመጠበቅ ዕለቱን እንዲያሳልፍ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለፃ የዘንድሮ በዓል የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በድል በተጠናቀቀበትና የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ስኬታማ በሆነበት ወቅት ላይ መከበሩ ልዩና ድርብ በዓል ያደርገዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው ሙስሊሙ ህብረተሰብ በህዳሴ ግድቡ ላይም ሆነ በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በተለይም የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ ለሆነው ለአካባቢው ሰላምና  ፀጥታ መረጋገጥ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት  ሼህ መሐመድ አብደላ በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ /አረፋ/ በዓልን ሲያከብር የታመሙትን በመጠየቅና የተቸገሩትን በመርዳት እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"የታመሙትን ስንጠይቅ ፤ የተቸገሩትን ስንረዳ  ከኮሮና በመከላከል፤ የአፍንና የአፍንጫ ጭንብል በመልበስ ሊሆን ይገባል" ብለዋል፡፡

ሙስሊሙ ህብረተሰቡ ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በመናበብና በመቀናጀት በሀገር ሰላምና ልማት ላይ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደቀጥልም  ተናግረዋል።

ሼህ መሐመድ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ  የሰላምና የፍቅር እንዲሁም የርስ በርስ ግንኙነት የሚጠናከርበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

ኢዜአ ካነጋገራቸው ሙስሊም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የገንደ ቆረሬ ነዋሪ አቶ ጀማል ሀሰን በሰጡት አስተያየት በኮሮና ምክንያት የኢድ በዓልን በለመዱት ደማቅ ስነስርዓት ማክበር ባይችሉም እራሳቸውን በመጠበቅ ባለቡት እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉም በዓሉን ሲያከብር እራሱን ከበሽታው ለመጠበቅ ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም