ወደውጭ ከተላኩ ሥጋ እና የወተት ተዋጽኦዎች 72 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

118

አዲስ አበባ ሐምሌ 23 /2012 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደውጭ ከተላኩ ሥጋ እና የወተት ተዋጽኦዎች 72 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ የሥጋ እና የወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለስላሴ ወረስ ለኢዜአ እንደገለጹት አብዛኛው ገቢ ከበሬ፣ ፍየል እና የበግ ሥጋ ምርት ውጤቶች የተገኘ ነው፡፡

ቀሪው ገቢ የተገኘው ደግሞ ከሌሎች እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ መሆኑን ጠቁመው በእዚህም ወተት፣ ማር፣ ሰም እና ዓሳ ወደ ውጭ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ እና በግንቦት ወራት ከኢትዮጵያ ወደ ዱባይ እና ሳዑዲ አረቢያ የተላኩት የዘርፉ ወጪ ንግድ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ አገራቱ የሚደረገው በረራ ከመቋረጡ በፊት በቀን የ100 ቶን የሥጋ ፍላጎት እንደነበር ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ "አገራቱ ሥጋና የሥጋ ውጤቶችን ከኢትዮጵያ ለማስገባት ፍላጎት አላቸው" ብለዋል፡፡

በኮሮናቫይረስ እና በእንስሳት እጥረት ሳቢያ የበረራ አገልግሎት መቋረጡ ኢትዮጵያ ከዘርፉ 124 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ያሰበችውን ዕቅድ ለማሳካት እንቅፋት እንደሆነባትም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአገር ውስጥ ፍላጎት መጨመር እና የእንስሳት ህገ-ወጥ ንግድ መበራከት ለዘርፉ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

አቶ ኃይለስላሴ እንደሚሉት ከእንስሳት አቅርቦት አንፃር የአገር ውስጥ ፍላጎት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱ ለዘርፉ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ድርሻ አለው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በማከል "ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት አንድ ኪሎ ግራም የበሬ ሥጋ ቢበዛ በአራት የአሜሪካ ዶላር የሚላክ ሲሆን በአገር ውስጥ ግን እስከ 10 የአሜሪካ ዶላር በሚደርስ ዋጋ ሊሸጥ ይችላል" ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሥጋ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ የአካባቢውን ገበያ እያማተሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ የዘርፉን ከፍተኛ አቅም ለመጠቀም የእንስሳት እርባታን፣ የእንስሳት ሕክምና አገልግሎቶችን መጨመር እና የገቢያ ተኮር ዋጋ አቅርቦት ሰንሰለቱ እንዲሻሻል ማድረግ እንደሚገባት ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡

"የሥጋ ምርቶችን በጥራት እና በመጠን ማቅረብ ከተቻለ አገሪቱ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ያስችላታልም" ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድ እና የአገር ውስጥ ገበያ አቅርቦቶችን ለማመጣጠን መንግስት በአገሪቱ አምስት የድንበር ኬላዎች የእንስሳት ማቆያ ግንባታ በማከናወን ላይ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አቶ ኃይለስላሴ አስረድተዋል፡፡

ባለሀብቶችም የራሳቸውን የእንስሳት ማቆያ እና ሌሎች መገልገያ ጣቢያዎችን እንዲገነቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ የቁም እንስሳት ባለቤት መሆኗ ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሥጋ ውጤቶችን በማቅረብ ከቀዳሚዎቹ አገራት ተርታ እንደሚያሰልፋት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም