በትግራይ ክልል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መሻሻል እያሳየ ነው

128
አክሱም ሚያዝያ 1/2010 በትግራይ ክልል ባለፉት ወራት የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በተሻለ መንገድ ማስፈጸም መቻሉን የክልሉ ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ። በፍትሕ ቢሮ የወሳኝ ኩነት ዋና ስራ ሂደት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ሃዋዝ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ71 ሺህ በላይ ልደት፣ ጋብቻ፣ ሞትና ፊቺ ተመዝግበዋል፡፡ ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም በክልሉ በሁሉም የከተማና የገጠር ቀበሌዎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በቋሚነትና ቀጣይነት ባለው መንገድ ለመስራት ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለአንድ አገር የመረጃ ምንጭ መሆኑን በልማት ቡድናቸው በሚያካሂዱት ውይይት ትምህርት ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በአክሱም ከተማ የንግስተ ሳባ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፍስሃ መለስ ናቸው፡ ይህንኑ መሠረት በማድረግም ልጃቸው በተወለደች በ90 ቀናት ውስጥ በማስመዝገብ የልደት ሰርቲፊኬት መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡ ጋብቻ ለመመስረት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማከሄዱን የተናገረው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ የሆነው ወጣት ዘሚካኤል ፍስሃ ነው፡፡ ወጣቱ እንዳላው በሚኖርበት አከባቢ በህብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ በመፈጠሩ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንደ ስርአት ሆኖ እየቀጠለ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም