የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ አፀደቀ

67

ሐምሌ 23 ጋምቤላ (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2013 ዕቅድ ማስፈጸሚያ 3 ነጥብ 377 ቢሊዮን ብር በጀትና የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ።

በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ውጤታማ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ጠንክረው እንዲሰሩም የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ላክደር ላክባክ ጠይቀዋል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ የ2012 የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም የጠቅላይ ፍርድ ቤትና የኦዲት ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ ለ2013 የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ ማስፈጸሚያ የቀረበለትን ሶስት ቢሊዮን 377 ሚሊዮን 653 ሺህ 415 ብር በጀት እንዲሁም አዋጆችንና ሹመቶችን አጽድቋል።

ከጸደቀው በጀት መካከል 2 ነጥብ 373 ቢሊዮን ብሩ ከፌዴራል መንግስት ድጎማና ከብድር የተገኘ ሲሆን ቀሪው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ከክልሉ የሚሸፈን እንደሆነም ተገልጿል።

ጉባኤው የአምስት የካቢኔ አባላት የ25 የጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛና የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመትና የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።

ትላንት ምሽት ጉባኤው ሲጠናቀቅ አፈ-ጉባኤው እንደገለጹት በክልሉ በተለይም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመስኖ የመንገድና የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተው ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት መስራት ይገባል።

በክልሉ የስራ እድል ፈጠራ እንቅስቃሴዎችን ይበልጥ በማስፋት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ጭምርም በተሻለ ደረጃ የሚሰራ መሆኑንም አመልክተው ምክር ቤቱ በክልሉ ሊተገበሩ የታሰቡ የልማት ስራዎች በአግባቡ እንዲቀጥሉ የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም