ኢትዮ-ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት ከ47 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ

58

አዲስ አዲስ  (ኢዜአ) ሐምሌ 23/ 2012 ኢትዮ-ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት 47 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ።

የተቋሙ ሠራተኞች ያሳዩት ቁርጠኝነት ኩባንያው ላስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።


ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ለህዝብ ይፋ ያደረገውን የሦስት ዓመት ስትራቴጂና የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግላጫ ሰጥቷል።

የኢቲዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮ ቴሌኮሙ በስትራቴጂው ትኩረት አድርጎ ከሰራባቸው ጉዳዮች አንዱ የኩባንያውን የፋይናንስ አቅም ማሳደግ ነው።

በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ 47 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን105 በመቶ ማከናወን መቻሉንም ገልጸፀዋል።

ለእዚህ ግብ መሳካት የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ያሳዩት ቁርጠኝነት የጎላ መሆኑንም ነው ሥራ አስፈጻሚዋ የተናገሩት።

እንደእሳቸው ገለጻ የዘንድሮ ዓመት ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸርም በ31 ነጥብ 4 በመቶ እድገት አሳይቷል።

የተሰበሰበው ገቢ ከሞባይል ድምጽ 49 በመቶ፣ ከዳታና ኢንተርኔት 29 በመቶ፣ ከዓለም አቀፍ ንግድ 9 መቶ ፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎቶች 9 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም ኬሎች አገልግሎቶች 3 ነጥብ 6 በመቶ ድራሻ ያለው መሆኑም ተገልጿል።

የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 147 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 107 በመቶ እንደሚሸፍን ተገልጿል።

ይህ ውጤት ካለፈው በጀት አመት ጋር ሲነጻጸርም የ50 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

የዕቅድ አፈጻጸሙ የላቀ እንዲሆን ካደረጉት ተግባራት መካከል አንዱ ኩባንያው የኔትወርክ ማስፋፊያና የአገልግሎት ጥራትን ለመጨመር የሚያስችሉ የ4ጂ አገልግሎትን በመላው አዲስ አበባ በማቅረቡ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለታክስ እና 4 ቢሊዮን ብር የኩባንያ የትርፍ ክፍያ ለመንግስት የከፈለ ሲሆን ለፕሮጀክቶች ብድር 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ክፍያ ፈጽሟል።

በአሁኑ ወቅት የኩባንያው የደንበኞች ብዛት 46 ነጥን 2 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከባለፈው ዓመት የ5 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማሳየቱ በመግለጫው ተመልክቷል።

ኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማጠናከርና ተወዳዳሪነቱን አስተማማኝ ለማድረግ ያስችለኛል ያለውን የሦስት ዓመት አዲስ ስትራቴጂ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለይ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በወቅቱም በ2012 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 45 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዶ ወደስራ መግባቱም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም