የጤና ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በአዳማ ችግኝ ተከሉ

70

አዲስ አበባ ሀምሌ 22/2012 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በአዳማ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል። አካባቢን አረንጓደ በማድረግ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል ተገልጿል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሳህረለ አብዱላሂ እንዳሉት በዘንድሮው ዓመት እንደ ጤና ሴክተር ክልሎችንና የፌዴራል ተጠሪ ተቋማትን በማስተባበር ከ6 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል።

በመርሐ-ግብሩ ማስጀመሪያ ቀን 35 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው፣ በዛሬው እለትም ከአምስት ሺህ በላይ ችግኞች እንደተተከሉ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ልማት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎችን ለመከላከል የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቅስዋል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ምክንያት እንደ ካንሰር ባሉ በሽታዎች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል።

ህብረተሰቡም ችግኞችን በሚተክልበት ወቅት ጎን ለጎን የጓሮ አትክልቶችን በመትከል ወደ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ለመግባት ምቹ እድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የክረምት ወቅት አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ነድፋ እየሰራች ትገኛለች። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም