በአውስትራሊያ በተከሰተ የሰደድ እሳት 3 ቢሊዮን ገደማ እንስሳት ለጉዳት መዳረጋቸው ተገለጸ

128

ሐምሌ 21/2012(ኢዜአ) በአውስትራሊያ እ.ኤ.አ ከ2019 እስከ 2020 ድረስ በተከሰተው የሰደድ እሳት 3 ቢሊዮን ገደማ እንስሳት ለሞትና ለስደት መዳረጋቸውን ወርልድ ዋይድ ፈንድ ፎር ነቼር በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት 143 ሚሊዮን አጥቢ እንስሳት፣ 2 ነጥብ 46 ቢሊዮን ተሳቢ እንስሳት፣ 180 ሚሊዮን አእዋፋት እና 51 ሚሊዮን እንቁራሪቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

ከአስርት ዓመታት ወዲህ የዚህ አይነት አስከፊ ሰደድ እሳት ባልተመዘገበበት ቃጠሎ ከ11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ የወደመ ሲሆን፤ በሰደድ እሳቱ 1 ነጥብ 25 ቢሊዮን እንስሳት ደግሞ ቀጥታ ተጎጂ ሆነዋል፡፡

ከተጎጂዎች መካከል የአውስትራሊያ መለያ የሆኑት ካንጋሮዎች እና ሌሎች በአውስትራሊያ ብቻ የሚገኙ እንስሳት ተጠቅሰዋል፡፡

በሰደድ እሳቱ ከመኖሪያቸው ወደ ሌላ ስፍራ የተሰደዱት እንስሳት ለምግብ እና መጠለያ እጥረት መጋለጣቸውም ነው በሪፖርቱ የተካተተው፡፡

ለዓመታት የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ከመስከረም 2019 እስከ መጋቢት 2020 የቆየው ሰደድ እሳት ለ34 ሰዎች ሞትና 3ሺ ቤቶች መቃጠል ምክንያት እንደነበርም ሮይተርስ አስታውሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም