በምእራብ ሸዋ ዞን ከ3 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ተተከለ

108

አምቦ፤ ሐምሌ 21/ 2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው የክረምት ወቅት ከ3 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መተከሉን የዞኑ እርሻ፣ ቡናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ጥራትና ግብይት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቶለሳ አራርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኞቹ የተተከሉት በ740 ሔክታር መሬት ላይ ነው።

የቡና ችግኞቹ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ዝርያዎች ናቸው ብለዋል።

በዞኑ 11 ወረዳዎች 3ሚሊዮን 201 ሺህ የቡና ችግኝ የተተከለ ሲሆን 12ሺህ 33 አርሶ አደሮች በስራው ተሳትፈዋል።

የዳኖ ወረዳ አርሶአደር ተሬሳ ደጋጋ በሰጡት አስተያየት በባለሙያ ምክር በመታገዝ ያዘጋጁትን የቡና ችግኞች የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም መትከላቸውን ተናግረዋል ።

ባለፉት ዓመታት ከተከሉት የቡና ችግኞች ተስፋ ሰጪ ምርት ማግኘት በመጀመራቸው ዘንድሮም በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው 12 ሺህ ችግኞችን ተክለዋል፡፡

ለተከሏቸው ችግኞችም አስፈላጊው እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

የኖኖ ወረዳ አርሶአደር ረቡማ ፈይሳ በበኩላቸው ከመደበኛ ሰብል ልማት ጎን ለጎን በተሻሻለ መንገድ ከ10ሺህ በላይ የቡና ችግኝ መተከላቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም