የሲዳማ ህዝብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራ መጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል... ርእሰ መስተዳድሩ

112

ሐዋሳ፤ ሐምሌ 21/2012 (ኢዜአ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ቀሪ ስራ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ሂደት ካለማንም ጎትጓችነት አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢዜአ እንዳሉት ግድቡ የሁላችንም አሻራ ያረፈበትና የጋራ ጥረታችን ውጤት ነው።

በተለይ የሃገሪቱን መፃዒ ዕድል ብሩህ የሚያደረግ ግዙፍ ፕሮጀክት በመሆኑ የሁሉም አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአካባቢው በተለያየ ጊዜ በተደረገው የንቅናቄ ስራ ሁሉም ዜጋ በሚባል ደረጃ የተቻለውን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሲዳማ ዞን በነበረበት ጊዜ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል ።

በድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት የነበሩ መንጠባጠቦችን በቀጣይ በማረም ድጋፉን ለማጠናከር የክልሉ መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል ።

በግድቡ ዙሪያ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ተቀናጅተው የሚሸርቡት የማደናቀፍ እንቅስቃሴ የሚያሳዝን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ከጠላት ተልዕኮ ወስደው የራሳቸውን እድል በራሳቸው እጅ እያበላሹ ያሉ የውስጥ ተላላኪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውኃ ሙሌት በስኬት በመከናወኑ ቀሪ ስራውን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ሂደት የክልሉ ህዝብ ያለማንም ጎትጓችነትና በራሱ ሙሉ ፍቃደኝነት የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

አስፈላጊ ከሆነ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ህዝቡ ዝግጁ መሆኑንም አቶ ደስታ ሌዳሞ ገልጸዋል።

የህዳሴው ግድብን አስመልክቶ በሃገር ደረጃ በታቀደ አግባብ የሚወርዱ ተግባራትን ተቀብለንና ከህዝብ ጋር ተወያይተን ተፈፃሚ በማድረግ ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም