ስፖርት ኮሚሽን በመሪ ዕቅዱ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ

312

አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2012(ኢዜአ) በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ስፖርት ኮሚሽን በመሪ ዕቅዱ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ። 

ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆነው የስፖርት መሪ እቅድ የክልል ስፖርት ሃላፊዎች፣ የስፖርት ማህበራት ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው እለት ውይይት ተካሂዶበታል።

 በውይይቱ ላይ መሪ አቅዱን ያቀረቡት በስፖርት ኮሚሽን የእቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ እንድሪስ አብዱ በኢትዮጵያ ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የስፖርት ፖሊሲ ተቀርፆ ሲሰራ ነበር።

ይሁን እንጂ በታዳጊዎች ምልመላ ስልጠና፣ የስፖርት ማህበራት ማደረጃና ስፖርቱን ህዝባዊ በማድረግ በኩል ተግዳሮቶች ነበሩበት።

ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም  የሚተገበረው የአስር ዓመት የስፖርት መሪ እቅድ እነዚህ ችግሮችና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን ተናገረዋል።

ስትራቴጂክ ዕቅድ ትኩረት ካደረገባቸው ዋና ዋና አንኳር ጉዳዮች መካከል የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የግሉ ዘርፍ በስፖርት ተሳትፎውን በማሳደግ በስፖርት ትጥቆች ማምረት ላይ በሰፊው እንዲሰማሩ በሚያበረታታና አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን በባህል ስፖርቶች በሰፊው በሚያሳትፍ  መልኩ መዘጋጀቱን ተናገረዋል።

እንዲሁም የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች የስፖርት ተሳትፎ ማሳደግ ላይ የ10 ዓመቱ መሪ እቅዱ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን እቅድ እውን ለማድረግ የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ስራ፣ ስፖርት ማህበራት በአዲስ መልክ ማደራጀትና የገንዘብ አቅማቸውን ማጎልበትና በትኩረት ይሰራል ተብሏል።

በመሪ እቅዱ ላይ የተሳተፉ ተወያዮችም አገራዊ መሪ እቅዱ ስፖርትን ህዝባዊ ለማድረግና ለመተግበር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውና ሊያሰራ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ እንደመብራትና ውሃ ለህብረተሰቡ አስላፈላጊ በመሆናቸው ትኩረት ተደርገው ሊሰሩ ይገባል ተብሏል።

ነገር ግን የስፖርት አካዳሚዎቻና ክልሎች ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ላይ እየሰሩ ነው።

ይህ ከሚሆን ግን ክልሎች ታዳጊዎች በማፍራት ላይ ከሰሩ የስልጠና አካዳሚዎች የብሄራዊ ቡድን ዝግጅት የሚካሄድበት ቦታ ቢሆን የሚመረጥ መሆኑን በመግለጽ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

እንዲሁም በዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና በቀጣና ደረጃ ኢትዮጵያ የምትወዳደርበት የስፖርት አይነት ቁጥር በመሪ እቅዱ ከተቀመጠው በላይ ከፍ ማለት እንደሚገባው አንስተዋል።

የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር መሪ እቅዱ በስፖርት ሴክተሩ ላይ ያሉ ችግሮች በጥናት ተለይተው በመሪ እቅዱ መካተታቸውን ተናግረዋል።

ይህን እቅድ ከግብ ለማድረስ የስፖርት አመራሮችና ባለሙያዎች የግል ፍላጎታቸውን ወደ ጎን በመተው መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።