በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው መዘናጋት የኮሮና በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል --ጤና ቢሮ

78

አዳማ፣  ሐምሌ 20/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በህብረተሰቡ ውስጥ በተፈጠረው መዘናጋት የኮሮና በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው የኮሮና በሽታ ስርጭት አሳሳቢነትን ለመግታት በክልሉ ከሚገኙ ዞኖችና ከተሞች የተውጣጡ ኮሙኒኬተሮች፣ከጤና ዘርፍ አመራሮችና የፌዴራል የሚዲያ ተቋማት ባለሙያዎች ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄዷል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሲስተር ሰዓዳ ዑስማን እንደገለጹት በህብረተሰቡ ውስጥ በተፈጠረው መዘናጋት የኮሮና በሽታ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ  ላይ ደርሷል።

በመጀመሪያ አካባቢ "ህብረተሰቡ ስለበሽታው የነበረው ጥንቃቄ ጥሩ ነበር" ያሉት ዳይሬክተሯ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ በተፈጠረው መዘናጋት አሁን ላይ አስከፊ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ በተፈጠረው  መዘናጋት  የበሽታው ስርጭት በክልሉ በቀን ከ69 እስከ 120 ሰው በቫይረሱ እየተያዘ እንደሚገኝና አዳዲስ ኬዞች እየተመዘገበ መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት 25 ሆስፒታሎች ለኮሮና ማከሚያ ማዘጋጀቱን የገለጹት ዳይሬክቴሯ፤ ከ370 በላይ ለይቶ ማቆያዎችም በክልሉ ዞኖችና ከተሞች መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ከኮሮና በሽታ ህክምና በተጓዳኝ መደበኛ የጤና አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉንም ዳይሬክተሯ አብራርተዋል ።

የመድረኩ ዓላማ አሁን እጅጉን እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮና በሽታ ስርጭት ለመቀነስ ባለፉት ወራት የነበሩ ሂደቶችን ለመፈተሽና ቀጣይ የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ናቸው።

በሽታው በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ ህጎች፣ መመሪያዎችና  የተሰጡ ትምህርታዊ  ግንዛቤዎች  የተፈለገውን  ያክል ውጤት  አላመጡም ብለዋል ።

በመድረኩ በህብረተሰቡ ውስጥ የታዩ ክፍተቶች በተለይም በትራንስፖርት ፣ ለቅሶ፣ ገበያ ቦታዎች፣ ሬስቶራንቶችና ካፍቴሪያዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት  የሚሰጡ  ተቋማትና ቤተ እምነቶች አካባቢ  በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልፀዋል ።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች የበሽታውን ስርጭት የሚያስፋፉ አሰራሮችን  በማጋለጥ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማነሳሳት መድረኩ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል ።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የባቱ ከተማ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ከድር ገመቹ በበኩላቸው በህብረተሰቡ ላይ ሰፊ መዘናጋት እንደሚታይ ጠቅሰው፤ በዚህም የበሽታው  ስርጭት  እየተስፋፋ በመሆኑ የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል ።

ለበክልሉ ከትምህርታዊ ግንዛቤ በተጓዳኝ በቤት  ለቤት ልየታና ክትትልም  ከ3 ሚሊዮን  በላይ አባወሯዎች ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ተጠቅሷል ።

በቅርቡ በክልሉ ጤና ቢሮ በተደረገው ጥናትም 46 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ብቻ ስለበሽታው አስከፊነት ግንዛቤ እንዳላቸው በመድረኩ ላይ ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም