ኢትዮጵያ ከ382 ሺሕ ሰዎች በላይ የኮሮና ቫይረስ መረመረች

134

   አዲስ አበባ ሀምሌ 20/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከ382 ሺሕ ሰዎች በላይ  የኮሮና ቫይረስ  መመርመሯን  ገለጸች፡፡

 በአለማችን በፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ በመመርመር የስርጭት አድማሱን ለመቀነስ ሀገራት ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ኢትዮጵያም  የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግስት ከወሰዳቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርመር  ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ስፍራ ሆናለች፡፡

እንደ የአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃ

 ኢትዮጵያ ከአህጉሪቱ በመርመር አቅም  ከደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮና ግብጽ በመቀጠል በአራተኛ ደረጃ ላይ ትግኛለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ  የኢትዮጵያን የመመርመር አቅም ለማሳደግ መሰራቱን በቲውተር  ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

የኮቪድ 19 ምርመራን አቅም ለማሳደግም ቃል ከተገባው  አንድ ሚልዮን ኪቶች መካከል የመጀመሪያውን ዙር ትናንት መቀበላቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

መመርመሪያውን ከለገሱት ተቋማት መካከል ግማሽ ያህሉን ያበረከተው  ሀገር በቀሉ ኩባንያ  በቅርቡም  በሀገር  ውስጥ ኪቶች ለማምረት ማቀዱን  ገልጸዋል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በአፍሪካ በኮቪ19 የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን በመጠጋቱ 844 ሺሕ 542 ሲደርስ  በዚያው ልክ ያገገሙትም  489 ሺሕ 948 ደርሷል።

የቫይረሱ ተጠቂዎቹን ቁጥር ለመለየትና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የመመርመር አቅምን ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ማዕከሉ እንዳስታወቀው፤ ከአፍሪካ 2ሚሊዮን 773 ሺሕ ሰው በመመርመር ደቡብ አፍሪካ በአንደኝነት ስትቀመጥ፤ ሞሮኮ አንድ ሚሊዮን 126 ሺሕ፣ ግብጽ 449 ሺሕ 968፣ ኢትዮጵያ 382 ሺሕ 339 ሰዎች በመመርመር  በደረጃ ተቀምጠዋል።

ከፍተኛ ምርመራ አድርገዋል ተብለው በተጠቀሱት አራቱ ሀገራት  312 ሚሊዮን 625 ሺሕ 857 ሰዎች ይኖራሉ፡፡

ከምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 14 ሀገራት ኢትዮጵያ 382 ሺሕ 339 ሰዎችን በመመርመር ቀዳሚ ናት።

ኬኒያ 276 ሺሕ 415፣ ኡጋንዳ 260 ሺሕ 465 ፣ ሩዋንዳ 242 ሺሕ 129 ሰዎች በመመርመር ከሁለት እስከ አራትኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን የማዕከሉ መረጃ ያመለክታል።

በአፍሪካ ይሄ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ 844 ሺሕ 542 ሰዎች በኮቪድ19 የተያዙ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 489ሺሕ 948ቱ አገግመው፣ 17ሺሕ 682ቱ ሞተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም