ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች ለሚወለዱ ህፃናት እድገት የተለየ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ተባለ

57
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2010 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ቤተሰቦች የሚወለዱ ህጻናትን የወደፊት ህይወት የተሻለ ለማድረግ ጤናማ እድገት የሚያገኙበት ሁኔታ ሊመቻች አንደሚገባ ተገለፀ። "ያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያካሄደው 5ኛው የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል። የዘንድሮው ጉባኤ በህፃናት ጤናማ እድገትና የተሻለ የወደፊት ህይወት  ላይ ያተኮረ ሲሆን በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያም ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል። በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ ዋና ተማራማሪ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ የጥናቱ ዓላማ ከደሃ ቤተሰብ የሚወለዱ ህጻናት ያሉባቸውን ፈተናዎች በማጤን የወደፊት እጣ ፋንታቸው የተሻለ ይሆን ዘንድ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች ማመላከት ነው። በጥናቱ መሰረት ድህነት ውስጥ ያሉ ህጻናት ለብዙ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል። ከነዚህም መካከል "መቀንጨር" በሚል የሚታወቀውና በተለይ ህፃናት በጨቅላ እድሜያቸው ማግኘት የሚገባቸውን የተመጣጠነ ምግብ በተገቢው መንገድ ባለማግኘታቸው የሚከሰተው የጤና እክል ዋነኛው እንደሆነም ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል። ይህ ችግር በአንጻራዊነት በስፋት የሚስተዋለው ከከተማ ይልቅ በገጠሩ የሀገሪቷ ክፍሎች መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ በተለይም በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ችግሩ በስፋት መኖሩም ተጠቁሟል። ከዚህም ሌላ በዚህ ህይወት ውስጥ የሚያልፉ ህጻናት የትምህርት ተሳትፎም በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑም በጥናቱ ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት የህጻናት ምርምር ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ይሰሃቅ ታፈረ እንደሚሉት በሀገሪቷ የሚገኙ የደሃ ቤተሰቦች ህፃናት ልጆችን እድገት ማሻሻል በሚቻልበት መንገድ ተከታታይ ጥናቶች ሲካሄዱ 15 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህንንም መሰረት በማድረግ ተግባራዊ እርምጃዎችን የሚወስድ ፕሮጀክት ከጥናቶቹ ጎን ለጎን ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው። በዚሁ የተቀናጀ ጥረት መሰረትም በመቀንጨር ችግር የሚሰቃዩ ህፃናት ህይወትን ማሻሻል መቻሉን ዶክተር ይስሃቅ ይገልፃሉ። ጥናቶቹን መሰረት በማድረግ የተቀረፀው ፕሮጀክት ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ከአንድ በመቶ ወደ 47 በመቶ እንዳሻቀበ ተናግረዋል። እንደዚሁም 45 በመቶ የነበረው ከመቀንጨር ጋር የተያያዘ ችግር ከፕሮጀክቱ ትግበራ በኋላ ወደ 38 በመቶ መቀነስ መቻሉም ተመልክቷል። እንዲያም ሆኖ ግን ከደሃ ቤተሰብ አብራክ የሚወጡ ህፃናት የወደፊት ማንነትና ህይወት በዘላቂነት የተሻለ አንዲሆንና ከሌሎች ዜጎች ጋር ተመሳሳይ አድል እንዲያገኙ ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። መሰረቱን በብሪታኒያ ኦክስፎርድ ያደረገው ፕሮጀክቱ በኢንግሊዝ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል። በፕሮጀክቱ አማካኝነት ተመሳሳይ ጥናቶች በህንድ፣ ፔሩ እና ቬትናም በመካሄድ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም