አመራሩ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመመከት ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራት አለበት...ብልፅግና ፓርቲ

64

ሆሳዕና ሐምሌ 19 2012 (ኢዜአ) አመራሩ ጸረ ሰላም ኃይሎችን በመመከት ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ በመስጠት መረባረብ እንዳለበት የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የሀድያ ዞን አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በሆሳዕና ከተማ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡

የክልሉ የኮንሰትራክሽን ቢሮ ኃላፊና የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ አቶ የማታአለም ቶኪሎ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት ፓርቲው በሀገሪቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ ነው ።

የክልሉ አመራር ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት መረባረብ አንደሚጠበቅበት አቶ የማታአለም አስገንዝበዋል ።

ያለአግባብ ስልጣን ይዞ ለመቆየት የሚፈልገው ህወሓት በክልሉ እጁን በማስገባት ቀድሞ ያልመለሰውን የአደረጃጀት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ ተጋምዶ የቆየውን ህዝብ ለመለያየት እያከናወነ ያለውን አፍራሽ ድርጊት በመቃወምና በመመከት አመራሩ ለህዝብ ጥቅም መረጋገጥ በፅናት እንዲቆም አሳስበዋል ።

የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ህገ መንግስታዊ ሂደቱን ተከትሎ ምላሽ እንደሚሰጠው የተናገሩት አቶ የማታአለም ተገቢ ምላሽ እስከሚሰጥ ድረስ አመራሩ ለህዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ቅድሚያ ሰጥቶ መረባረብ እንዳለበት ገልፀዋል ።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ በበኩላቸው የመድረኩ ዓላማ አመራሩ በአመለካከትና በተግባር አንድነቱን እንዲያጠናክር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ።

ሀገሪቱን ወደ ከፍታ የሚወስዱ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ባሉበት ወቅት ህወሓት የህዝቡን የአደረጃጀት ጥያቄ ሰበብ እድርጎ ልዩነት ለመፍጠርና ወደ ትርምስ እንድንገባ እየሰራ መሆኑን ተረድተን በጋራ ልንመክተው ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ህዝብ ብስለት በተሞላበት ሂደት ጠብቆ ያቆየውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም ለህዝብ ተጠቃሚነት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል ።

ትናንት ተጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሔደው የውይይት መድረክ ላይ ከዞን እስከ ወረዳ ባለው እርከን የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም