ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 58 ቢሊዮን ዶላር አገኘች

68
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2010 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 11 ወራት ጊዜ ውስጥ ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ። ገቢው ከእቅዱ ግማሽ ያህል ነው ተብሏል። በበጀት አመቱ አስራ አንድ ወራት ሀገሪቱ ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 72 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዳ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ዛሬ ለኢዜአ ገልጿል። በበጀት ዓመቱ የግብርና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ምርቶች የወጪ ንግድ ካለፈው ዓመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነበር ተብሏል። ሚኒስቴሩ አንዳለው በተጠቀሰው የበጀት ዓመቱ ወራት ጊዜ ውስጥ ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 1 ነጥብ 97 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር እድገት አሳይቷል። ከማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከ418 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ያመለከተው ሚኒስቴሩ ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ53 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንዳለው ጠቅሷል። የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ሻይ ቅጠል፣ ጫት፣ ባህርዛፍ እና የቅባት እህሎች በአስራ አንድ ወራቱ የወጪ ንግድ ከ75 በመቶ በላይ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች ናቸው። ቡና፣ አበባ፣ ዱቄት፣ ቆዳ፣ ሙጫና እጣን እንዲሁም አትክልት፣ ፍራፍሬና የጥራጥሬ እህሎች ከ50 እስከ 75 በመቶ ክንውን የተመዘገበባቸው መሆኑም ተገልጿል። ሚኒስቴሩ አንደገለፀው የሀገሪቱ የወጪ ንግድ በታቀደው መሰረት ለመከወን እንቅፋት ከሆኑት ችግሮች መካከል ህገ-ወጥ ንግድ፣ የኩባንያዎች ከአቅም በታች መስራት እና የምርት ጥራት ጉድለት በዋናነት ይጠቀሳሉ። የወጪ ንግዱን ለማጠናከር የግብርና ምርቶችን በጥራት በማዘጋጀት በከፍተኛ መጠንና በጊዜው ለገበያ የሚቀርብበትን ሁኔታ መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑም ተመልክቷል። በወጪ ንግዱ ዘርፍ የሚስተዋለውን ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የግብይት ውድድር በመከላከልና የዓለም ገበያ የሚጠይቀውን የተወዳዳሪነት መስፈርት በማሟላት የተቀባይ አገራትን ይሁንታ ለማግኘት ሰፊ ስራዎች አንደሚጠበቁም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም