በአጥንትና ድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል እየተሰራ ነው

77
አዲስ አበባ ሀምሌ 3/2010 በአጥንትና ድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የአጥንት ህክምናና የአደጋዎች ህክምና ስፔሻሊስቶች ብሄራዊ ማህበር አስታወቀ። የኢትዮጵያ የአጥንት ህክምናና የአደጋዎች ህክምና ስፔሻሊስቶች ብሄራዊ ማህበር 13ኛውን ዓመታዊ ሳይንሳዊ ጉባኤ እያካሄደ ነው። ጉባኤው በአደጋዎችና በግጭቶች ወቅት የሚከሰቱ ጉዳቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ህክምና ለመስጠትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብሩክ ላምቢሶ፤ በኢትዮጵያ የአጥንት ህክምና ራሱን ችሎ መሰጠት ከጀመረበትና ሥልጠናውም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዲፓርትመንት ተከፍቶ ባለሙያዎችን ማፍራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ የህክምናው ፍላጐቱ እየጨመረ መጥቷል። የህክምና አሰጣጡ እና በሙያው የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር ከፍላጐቱ ጋር ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ብሩክ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በህክምና ዘርፉ የሚያሰለጥኑ ተቋማት እና በሙያው መሰልጠን የሚፈልጉ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል። ህክምናውን የሚያግዙ መሳሪያዎችና ህክምናውን የሚሰጡ የግል ሆስፒታሎች መፈጠርም ለአጥንት ህክምና አገልግሎት መሻሻል ሰፊ እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በአጥንት ህክምና ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ተማሪዎች በመሆናቸው በሚቀርቡ ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ በሚደረግ  ውይይት በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ትልቅ እድል እንደሚፈጥርም ጭምር ነው ዶክተር ብሩክ የጠቆሙት። ዶክተር ብሩክ ለአጥንት ህክምና የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች በመንግስት በኩል ግዢ እየተፈፀመና በአገር ውስጥም ለማምረት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያት በውጪ አገራት ሄዶ ለመታከም የሚወጣው ወጪን እንደሚያስቀረው ነው የተናገሩት። በድንገተኛ አደጋ ህክምና ያለውን አገልግሎት ለማሻሻልም የአየር አንቡላንስ አገልግሎት አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ላይም የተግባር ስራዎች እየተሞከሩ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት። በጉባኤው የክብር እንግዳ በመሆን የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚን አማን በበኩላቸው፤ አገሪቱ ቀስ በቀስ ወደ ዘመናዊ የአጥንት ህክምና ተጠቃሚነት እየተሸጋገረች እንደምትገኝ ገልፀዋል። የአጥንት ህክምና ሀኪሞች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በመግለጽ ወደፊት በአዲስ አበባና በክልሎች የሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ ያለውን የአጥንት ህክምና በማጠናከር ለህክምና ወደ ውጪ የሚጓዙ ህሙማንን ለማስቀረት እንደሚሰራም ተናግረዋል። በጉባኤው ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የቦንብ ፍንዳታ በተከሰተበት ወቅት  በከተማዋ ባሉ ሆስፒታሎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊው እርዳታ ሲሰጡ ለነበሩ የህክምና ባለሙያዎችም የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ማህበሩ 130 ስፔሻሊስት ሀኪሞችና 130 የስፔሻሊስት ህክምና ተማሪዎች አባላት ያሉት ሲሆን በአጠቃላይ 260 አባላቶች እንደሆኑ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም