የከተሜነት ምጣኔውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማገዝ ያሻል ተባለ

117
አዲስ አበባ ሰኔ 3/2010 በአፍሪካ አገራት በፍጥነት እያደገ ያለውን የከተሜነት ምጣኔ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምራት እንደሚገባ ተገለጸ። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ከኮሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለዘመናዊና ውብ ከተሞች ሚና" በሚል ዐውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ የከተማ ፕላን ችግር፣ የተቋማት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት አለመስጠት፣ የቤትና መሬት አቅርቦት ችግር፣ የፍሳሽ አወጋገድና መሰል ችግሮች በፍጥነት እያደገ ያለውን የከተሜነት ምጣኔውን እየፈተኑት ነው ብለዋል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ ድህነትና የስራ አጥነት ችግር እንዳለ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ከተሜነትን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመምራት የከተሜነት ምጣኔውን ማሳለጥ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ከተሜነት ላለፉት ዓመታት ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን ገልጸው፤ አሁን ግን ከአገሪቷ አጠቃላይ ዕድገትና ፈጣን ከተሜነት ከወዲሁ በስርዓት ካልተመራና በየደረጃው ካልተፈታ ችግሩ ይበልጥ እየተወሳሰበ እንደሚሄድ ነው ስጋታቸውን የተናገሩት። ስለሆነም መልካም አስተዳደር የሰነፈነባቸው የዘመናዊና ውብ ከተሞች አካባቢ መገንባት የቅንጦት ሳይሆን ወቅቱ የሚፈልገው ወሳኝ እርምጃ መሆን እንዳለበትም ነው ያብራሩት። ከዚህ በፊት የተቀናጀ የከተሞች የመረጃ ስርዓት ለመዘርጋት የተጀመረ ስራ መኖሩን ጠቁመው፤ በቀጣይም ጅምሩን የሚያጠናክር ስራ ለመስራት በደቡብ ኮሪያ መንግስት ድጋፍ የአዋጭነት ጥናት ለማድረግ ፕሮጀክት መቀረጹን ገልጸዋል። የካዳስተር ወይም የመሬት መረጃ ስርዓት፣ የግብር አሰባሰብ፣ የሶፍት ዌር ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች በከተሞች ከተቀረጹ የከተሞች የተቀናጀ የመረጃ ተግባቦት ስርዓት ለመዘርጋት ከሚሰሩ ስራዎች መካከል ለአብነት አንስተዋል። የቀድሞው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርና በደቡብ ኮሪያ የሶስተኛ ድግሪያቸውን በመከታታል ላይ የሚገኙት አቶ መኩሪያ ኃይሌ፤ የውብ ከተሞች ወይም 'ስማርት ሲቲ' ጽንሰ ሐሳብ ከተሞች ሁሉንም አገልግሎታቸው በዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማገዝ ላይ ያጠነጠነ ነው ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ዕድገትና ልምድ ካላት ኮሪያ የመጣው ልዑካንም የከተሞቻችን ነባራዊ ሁኔታ ለመገምገምና በቀጣይ እንዴት መስራት እንደሚቻል፣ በአይ ሲ ቲ ዘርፍ የሰው ሃይል ማፍራትና የኮሪያ ቴክኖሎጂ የዕውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ያለመ ዐውደ ጥናት ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ሚስተር ሊም ሆኒም በበኩላቸው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለደቡብ ኮሪያ ዘላቂ እድገት ፋይዳው የትየለለ እንደነበር ገልጸው፤ የኮሪያን ተሞክሮ በአፍሪካ ከተሞች መተግበር ወሳኝ ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል። በፍጥነት እድገት ላይ ላለው የአፍሪካ የከተሞች ምጣኔም በማህበረ ኢኮኖሚ ዕድገቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠርና ውብ ከተሞች ለመገንባት ኮሪያ ድጋፏን አጠናክሯ እንደምትቀጥልም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል። በደቡብ ኮሪያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ዲኦክ ሱን ይም ከተሜነት እንደየአገሩ የሕግ ማዕቀፍ ተደራሽና ተመጣጣኝ በሆኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች መደገፍ እንዳለባቸው ይገልጻሉ። ከተሞችም በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አገልግሎታቸውን ማሳለጥ እንዲችሉ፤ በቅድሚያ ከአካባቢው ጋር የተጣጣሙ የአይ ሲ ቲ  መሰረተ ልማት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል። በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ባዩ የ'ውብ ከተሞች' ጽንሰ ሃሳብ የከተማው እንቅስቃሴ ፍሰት፣ ኢኮኖሚውና ነዋሪው ያለው ቁርጠኝነትና ውህደት እንደሆነ ገልጸው፣ የቴሌኮምና የአይ ሲ ቲ መሰረተ ልማትና አገልግሎቶች ለውብ ከተማነት መሰረት እንደሆነም ይናገራሉ። ውብ ከተሞችን ለመመስረት ተመራጭ መሰረተ ልማቶች መቅደም እንዳለባቸው የሚስማሙት ዶክተር አብዮት፤ በአንድ ጊዜ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ፖሊሲ ቀርጾ ማህበረሰባዊና ተቋማዊ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ለዚህም በኢትዮጵያ ዝግጁነት ቢኖርም በአይ ሲ ቲ የሚመሩ ውብ ከተሞችን ለመገንባት ግን ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት። በዐውደ ጥናቱም የቴክኖሎጂ ኮሜርሻላይዜሽን ለተመራጭ ከተሞች የሚኖረው ፋይዳ፣ መረጃና ልምድ ልውውጥ፣ ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ከተሞች ያለው ዕድገትና ፈተናዎች፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታና የፖሊሲ ጉዳዮች ጠቃሚ ሃሳቦች ይንሸራሸራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም