የህንዱ ግዙፍ አየር መንገድ 10 ከመቶ ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ ገለፀ

61

ሐምሌ 14/2012(ኢዜአ) ግዙፉ የህንድ አየር መንገድ ኢንዲጎ ኮሮና ቫይረስ ባሳደረሰው ጫና የበረራ ፍላጎት በመቀነሱ 10 ከመቶ ሰራተኞቹን እንደሚቀንስ ነው የገለፀው፡፡

ኢንዲጎ አየር መንገድ ባጋጠመው ከፍተኛ የገቢ መቀነስ ሳቢያ እስከ 420 ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ ወጪ ለመቀነስ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

የኢንዲጎ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ራኖሮይ ዱታ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የኩባንያውን ሕልውና ለማስቀጠል አንዳንድ መስዋእትነቶችን ለመክፈል መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የአየር መንገዱን 10 ከመቶ ሰራተኞች ለመቀነስ ታቅዷል ብለዋል፡፡

የወረርሺኙን መሰራጨት ተከትሎ ለወራት ያለ ስራ የቆመው ኢንዲጎ አየር መንገድ 24 ሺህ ሰራተኞችን በስሩ አቅፏል፡፡

በሀገሪቱ 48.9 ከመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው የሚነገረው ኢንዲጎ ባለፉት አስር አመታት በተከታታይ ትርፍ አስመዝግቦ ነበር፡፡

በአለም ዙሪያ ያሉ በርካታ አየር መንገዶች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የጉዞ ገደቦች በመደረጋቸው ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑ ይታወሳል፡

አለም አቀፉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት የበረራዎች መቀነስ በዚህ ዓመት አየር መንገዶችን ከ 84 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊያሳጣ እንደሚችል አስጠንቅቋል ፡፡

አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በበኩሉ የአየር መንገዶች ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ወደ 419 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ሊል እንደሚችል ተናግሯል፡፡

አለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር 290 አባል አየር መንገዶች አሉት፡፡

ምንጭ፡ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም