በምዕራብ ጎንደር ዞን ለውጭ ገበያ ከቀረበ ሰሊጥ ከ102 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

81
ጎንደር ግንቦት 3/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን ለውጭ ገበያ ከቀረበ ሰሊጥ ከ102 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የዞኑ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ። የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ ከተማ ልማት መምሪያ የንግድ ኢንዱስትሪ ገበያ ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ክብረት ሙጨ ለኢዜአ እንደገለጹት የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የሰሊጥ ምርት ለገበያ የቀረበው ከጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ለውጭ ሀገራት ገበያ የቀረበው የሰሊጥ ምርት 73 ሺህ 382 ቶን ሲሆን ከዚህ ውስጥም 20 ሺህ ቶኑ ደረጃ ሁለት መሆኑን ገልፀዋል። ሰሊጡ ለገበያ የቀረበው በዞኑ ባሉ ሦስት የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች ህጋዊ ፈቃድ በተሰጣቸው ከ500 በላይ ነጋዴዎችና 25 የሕብረት ሥራ ማህበራት አማካይነት ነው፡፡ አቶ ክብረት እንዳሉት ለገበያ የቀረበው የሰሊጥ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ12 ሺህ ቶን ብልጫ ያለው ሲሆን ጥራቱም የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም " የምርት ጥራቱንና መጠኑን ለማሳደግ በሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመሰጠቱና ከማምረት ሂደት ጀምሮ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ አርሶ አደሩ በጥራቱ ላይ በትኩረት እንዲሰራ በመደረጉ ነው” ብለዋል። በተለይ ሰሊጥን ለረጅም ጊዜ ከማከማቸት ይልቅ በወቅቱ ለገበያ እንዲቀርብ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን  አመልክተዋል። በቀሪ ወራትም ከ20 ሺህ ቶን በላይ ሰሊጥ ለገበያ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ ክብረት ተናግረዋል። በመተማ ወረዳ ኮኪት ከተማ የሰሊጥ ምርት ሰብሳቢና አቅራቢ አቶ አሊ ሰይድ እንደተናገሩት ጥራት ያለው የሰሊጥ ምርት በመሰብሰብ ለገበያ ማቅረባቸው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ አምራቾችም በምርት ጥራት አጠባበቅና አያያዝ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እየያዙ መምጣታቸው የተሻለ ጥቅም እያስገኘላቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ የመተማ ወረዳ ሕብረት ሥራ ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ሲሳይ በበኩላቸው በወረዳው ከአርሶአደሩ የሰሊጥ ምርት በማሰባሰብ ለገበያ የሚያቀርቡ ማህበራት ቁጥር ባለፉት አራት ዓመታት ከአራት ወደ ስምንት ከፍ ብሏል፡፡ በወረዳው 19 ሁለገብ የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውን ገልጸው፣ የሰብል ምርት በወቅቱ ለገበያ በማቅረብ በኩል ክፍተት መኖሩንና ይህን ለማስተካከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ "በመተማ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማህበር አማካኝነት የተሰጠኝን የሰሊጥ ጥራት አጠባበቅ ትምህርት በመተግበር የተሻለ ምርት በማምረት ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ያሉት ደግሞ በወረዳው የመቃ ቀበሌ አርሶ አደር ሙሉነህ ፈለቀ ናቸው፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን በመጪው መኸር  ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ልማት በመሸፈን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሰራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም