የአፍሪካ ሀገራት በህገ ወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴ በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር ያጣሉ፡- ተመድ

83
አዲስ አበባ ሀምሌ 3/2010 ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ ህገወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀኃፊ ጥሪ አቀረቡ። ሁለተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአፍሪካ ህብረት የጋራ ጉባኤ በአዲስ አበባ  ታካሂዷል። ዋና ፀኃፊው አንቶኒዮ ጉተሬስ በጉባኤው ላይ እንዳሉት በአፍሪካ የገንዘብ ማሸሽ፣ታክስ ማጭበርበርና በሌሎች መሰል ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው። ሚስተር ጉተሬዝ በዚሁ ወቅት አንዳሉት የአፍሪካ ሀገራት በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የታክስ ማጭበርበርና የገንዘብ ማሸሽ ተግባራት ሳቢያ በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር ያጣሉ። ይህን የመሰለውን ኃብት ከጥፋት በማዳን ለአህጉሪቱ ልማት እንዲውል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እነዚህን ወንጀሎች እንዲከላከል ዋና ፀኃፊው ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የአፍሪካ ህብረት በአውሮፓዊያኑ 2018  “ሙስናን መዋጋት - ለዘላቂ የአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን ሁነኛ መንገድ” በሚል መርህ ሙስና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። የተመድ ዋና ፀኃፊም የአፍሪካ ህብረት ሙስናን ከአህጉሪቱ ለማፅዳት ትኩረት መስጠቱ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ከአህጉሪቱ በየዓመቱ የሚጠፋውን ሀብት እንዲታደግ አሳስበዋል። ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ለመከላከልም የገንዘብ ተቋማትና መንግስታት ከህገወጦች ጋር እንዳይተባበሩና ጠንካራ ህጎችን እንዲያወጡ ጠይቀዋል። የተመድና የአፍሪካ ህብረት የጋራ ጉባኤ ከህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ፈተናዎች ባሻገር ሰላምና ፀጥታን ጨምሮ በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይም ተነጋግሯል። ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ በተለይ በኢትዮያና ኤርትራ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች መካከል የተጀመረው ጥረት አፍሪካዊያን  ሰላምና ፀጥታን ለማጠናከር ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክት ነው ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ዘላቂ ምጣኔ ኃብታዊ ልማትን ለማረጋገጥ ታልመው ተግባር ላይ የዋሉትን የተመድ 2030 እና የአፍሪካ ህብረት 2063 የልማት አጀንዳዎች ለማሳካት ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም