የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

103

አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012(ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 87ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በገንዘብ ሚኒስቴር በቀረቡ የተለያዩ የብድር ስምምነቶች የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው።

ሁለቱ የብድር ስምምነቶች የተደረጉት ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር ሲሆን ዓላማቸውም ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የበጀት ድጋፍ ፕሮግራምና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ማስፈጸሚያ የሚውሉ ናቸው።

ሶስተኛው የብድር ስምምነት ደግሞ ከዳንስኬ ባንክ ጋር የተደረገ ሲሆን ለአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ነው።

ሶስቱም የብድር ስምምነቶች አነስተኛ /ከአንድ በመቶ በታች/ ወለድ የሚታሰብባቸው፤ የረጅም ጊዜ እፎይታ ያላቸውና በ40 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆኑ ከአገሪቷ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ይጸድቁ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

ምክር ቤቱ የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይም የተወያየ ሲሆን አገራዊና አካባቢያዊ ሠላም፣ ደህንነትና ጸጥታ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ በአገረ-መንግስትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ቀጣናዊ ትስስርና ትብብር ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ፤

በተጨማሪም ቁልፍ በሆኑ ፖሊሲዎች ላይ ጥናቶች በማካሄድ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ፣ ስትራቴጂያዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንተና መስጠትና ለውሳኔ የሚረዱ የቅድሚያ ግምቶች ማሳየት፣ የዳታ ክምችትና የእውቀት ቋቶችን ማደራጀት ከኢንስቲትዩቱ የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው። 

በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት የተወያየው ምክር ቤቱ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል። 

የኢንቨስትመንት ረቂቅ ደንብም ሌላው ምክር ቤቱ የተመለከተው ጉዳይ ነው። 

በቅርቡ የጸደቀውን የኢንቨስትመንት አዋጅ በአግባቡ ማስፈጸም ይቻል ዘንድ እንዲሁም በአጠቃላይ የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፉ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብ ማድረግ፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በግሉ ዘርፍ ሊሳተፉ የሚችሉባቸውን የኢንቨስትመንት ሥራዎች በመከለስ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ፤ የሥራ ፈጠራን ለማበረታታት፤

በቴክኖሎጂና በክህሎት ሽግግር ላይ ያለውን ሚና ማሳደግ፣ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙትን የመንግስት አገልግሎቶች በመሰብሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የኢንቨስትመንት አስተዳደርና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመን፣ የኢንቨስትመንት ማነቆ ለሆኑ ጉዳዮች መፍትሔ በመስጠት የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረግ፤

እንዲሁም ግልጽና ውጤታማ የባለሀብቶች ቅሬታ የሚስተናገድበት ሥርዓት ማበጀት በሚያስችል መልኩ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም