በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ከግጭት አነሳሽ መልዕክቶች ይልቅ ለአገር ሰላምና አንድነት እገዛ ማድረግ ይኖርባቸዋል - ኦባንግ ሜቶ

100

አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012(ኢዜአ) ''በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አገር ውስጥ ያለውን ህዝብ "ተነስ ውጣ" ከሚሉ የግጭት አነሳሽ መልዕክቶች ይልቅ ለአገር ሰላምና አንድነት የሚጠቅሙ ስራዎች ላይ እገዛ ማድረግ ይኖርባቸዋል'' ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ተናገሩ።

በተለያዩ አለም አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአገሪቱ ልማት፣ ዴሞክራሲና ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

በዚያው ልክ በአገሪቱ ያለውን ሰላም ለማደፍረስ ከውጭ ሆነው 'ተነስ ውጣ' የሚል ግጭት ቀስቃሽ መልዕክት በማስተላለፍ ስራ ላይ የተጠመዱ ጥቂት ሃይሎች መኖራቸው ግልጽ ነው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ግጭት የሚቀሰቅስ መልዕክት በማስተላለፍ ስራ የተጠመዱ ኃይሎች ጉልበታቸውን ለአገር ሰላምና ልማት ማዋል አለባቸው።

ለግጭትና ለሌሎችም እኩይ ተግባራት ማነሳሳት ፍጹም ከኢትዮጵያዊነት የራቀ ድርጊት መሆኑንም ተናግረዋል።

በስሜት ከመነዳት ይልቅ መልካም አስተሳሰብና ከውስጥ የሚመነጭ በጎ ምግባር ለአገር ጠቃሚ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን እንጂ ማባባስ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ለዚህም ተቀራርቦ መነጋገር፣ መደማመጥና መተማመን ትክክለኛው አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

''ከመከፋፈል፣ እርስ በርስ ከመገዳደል፣ ንብረት ከማውደም የሚገኝ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም'' ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፤ የአገሪቱ ሃብት ለሁሉም የሚበቃ እንደሆነ አስረድተዋል።

በአውስትራሊያ ሜልቦርን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በጋምቤላ ክልል ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለሌሎችም ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ ማህበረሰቦች የ100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ''ድጋፉ የኢትዮጵያዊነትና የሰብአዊነት መገለጫ ነው'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም