በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ዛሬ ቤልጂየምና ፈረንሳይ ይጋጠማሉ

98
አዲስ አበባ  3/2010 ዛሬ በዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍጻሜ ቤልጂየምና ፈረንሳይ ለፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠበቅ ነው። በሩሲያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 21ኛው ዓለም ዋንጫ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሮ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ ደርሷል። የመጀመሪያው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ 64 ሺህ 287 ተመልካች በሚያስተናግደው ሴይንት ፒተርስበርግ ስታዲየም ዛሬ በቤልጂየምና ፈረንሳይ መካከል ከምሽቱ ሶስት ሰአት ላይ ይደረጋል። ሁለቱ ጎረቤት አገሮች በባህል፣ ታሪክና ቋንቋ ያላቸው ትስስር የጠነከረ በመሆኑ የዛሬው ጨዋታ ከእግር ኳሱ ባለፈ ተጨማሪ ሌሎች ገጽታዎች ያሉት ነው። በሩብ ፍጻሜው ቤልጂየም ብራዚልን ፈረንሳይ ኡራጋይን በማሸንፍ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል። በጨዋታው ዙሪያ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ስፔናዊው የቤልጂየም አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ቡድናቸው ያለ ምንም ፍርሃት ጨዋታውን በማድረግ ፈረንሳይን አሸንፎ ወደ ፍጻሜው ለማለፍ የሚያስችል ጠንካራ ስነልቦና ተጫዋቾቹ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል። ''በቡድኔ ተጫዋች ውስጥ ፍርሃት ካለ የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት አንችልም ተጫዋቾቹ ያለ ምንም ፍርሃትና ጫና የሚጫወቱ ከሆነ በጨዋታው የምንፈልገውን ውጤት ማግኘት እንችላለን'' ብለዋል። የተጋጣሚው ቡድን የፈረንሳይ ቡድን በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቦታዎች ላይ ሚዛኑን የጠበቀ በመሆኑ ቡድናቸው በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ እንደሚጫወት ተናግረዋል። የተማሏ የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ ያለው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ለቤልጂየም ተከላካይ ክፍል ፈተና እንደሚሆን ገልጸው ለዚህም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዳደረጉ የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ ማርቲኔዝ አስረድተዋል። እ.አ.አ በ1998 የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በአገሩ ያዘጋጀውን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን ቡድኑን በአምበልነት የመራው የተከላካይ መስመር ተጫዋች የነበረውና የአሁኑ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሾው ነው። የ49 ዓመቱ አሰልጣኝ ከጨዋታው በፊት በሰጡት አስተያየት በጨዋታው የሚገኙ አጋጣሚዎችን በመጠቀምና ግብ በማስቆጠር ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ እንደሚደርሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ''ተጋጣሚያቸው ቤልጂየም እዚህ የደረሰችው በእድል እንዳልሆነና በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ብራዚልን ያሸነፈችበት የጨዋታ እቅድ ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሆን ነው'' ብለዋል። የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ለሚያደርጋቸው ማንኛውም የታክቲክና የቴክኒክ ለውጦች ቡድናቸው ዝግጁ እንደሆነና ተጋጣሚያቸው ከብራዚሉ ጨዋታ የተለየ የአጨዋወት ስልት ይዞ ወደሜዳ ሊገባ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ የሆነው ፈረንሳዊው ቲዬሪ ሄንሪ በዛሬው ጨዋታ ከአገሩ በተቃራኒ ወገን በመሆን የሚገጥማቸው እንደሆነ አውስተዋል። ፈረንሳዊው ቲዬሪ ሄንሪ በ1998 ዓለም ዋንጫ ከዲዲየር ዴሻምፕ ጋር መጫወቱ ይታወሳል። ''ለሄንሪ የዛሬው ጨዋታ በጣም ከባድ ስሜት የሚፈጥርበት ነው ምክንያቱም አገሩን ነው የሚገጥመው ይሄንን በሚገባ እገነዘባለሁ'' ብለዋል። ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በአጠቃላይ 73 ጊዜ ተገናኝተዋል። ቤልጂየም 30 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ስትይዝ ፈረንሳይ ደግሞ 24 ጊዜ አሸንፋለች ቀሪውን 19 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቤልጂየምና ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1904 ሲሆን በጨዋታው ቡድኖቹ ሳይሸናነፉ ሶስት አቻ በሆነ ውጤት መለያየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በዓለም ዋንጫ መድረክ ሲገናኙ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ቡድኖቹ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ፈረንሳይ የበላይነቱን ይዛለች። እ.አ.አ በ1938 ፈረንሳይ ባዘጋጀችው ሶስተኛው የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ ቤልጂየም ሶስት ለ አንድ ያሸነፈች ሲሆን ሜክሲኮ እ.አ.አ በ1986 ባዘጋጀችው 13ኛው ዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ ቤልጂየምን አራት ለሁለት አሸንፋለች። በዓለም እግር ኳስ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ስማቸው የሚጠሩ ተጫዋቾችን የያዙት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ለእግር ኳስ አፍቃሪው መዝናትን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ከቤልጂየም በኩል የማንችስተር ሲቲው ኬቨን ዴብሮይን፣ የቼልሲው ኤዲን ሀዛርድና የማንችስተር ዩንይትዱ ሮሜሎ ሉካኩ ከፈረንሳይ በኩል የአትሌቲኮ ማድሪዱ አንቶዋን ግሪዝማን፣ የፒኤስጂው ኬይለን ምባፔና የቼልሲው ኦሊቪየር ጂሩድ በዛሬው ጨዋታ የሚጠበቁ ናቸው። የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ የ41 ዓመቱ ኡራጓዊ አንድሬስ ኩንሀ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። የቤልጂየምና የፈርንሳይ አሸናፊ ነገ ከሚካሄደው ከክሮሺያና እንግሊዝ አሸናፊ ጋር የዓለም ዋንጫን ለማንሳት ይፋለማል። ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ.ም የተጀመረው የዓለም ዋንጫ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሞስኮው ሉዚኒስኪ ስታዲየም በሚደረግ የፍጻሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም