የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ችግኝ ተከላ ተካሄደ

51

ነቀምቴ  ሐምሌ 08/2012 (ኢዜአ) በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ተካሄደ።

በተከላው መርሃ ግብር የከተማዋ ከንቲባ አቶ በሪሶ ተመስገን እንዳሉት በአገሪቷ የአረንጓዴ አሻራን እውን ለማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃግበር እንደተጠበቀ ሆኖ የዛሬውን ልዩ የሚያደርገው በቅርቡ የተሰዋው አርቲስት ሃጫሉን ለማስታወስ በስሙ በተሰየመው ፓርክ የሚካሔድ መሆኑን አስታውቀዋል።

በነቀምቴ  ከተማ ዳርጌ ክፍለ ከተማ በተሰየመው በዚሁ ፓርክ በዛሬው እለት ከ10 ሺህ በላይ ችግኝ መተከሉንም ከንቲባው ተናግረዋል ።

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ለኦሮሞ ህዝብ ብሎም ለኢትዮጵያዊያን አንድነትና እኩልነት የታገለ ጀግና የኦሮሞ ልጅ በመሆኑ  ዛሬ በስሙ የተተከለው ችግኝ አስፈላጊው እንክብካቤ ተደርጎለት ስሙ ለዘላለሙ እንዲታወስ እንደሚደረግም አቶ በሪሶ  ገልፀዋል ።

የነቀምቴ ከተማ ክላስተር የግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረጋሳ ሞሲሳ በበኩላቸው ለአርቲስቱ ተብሎ በተሰየመው አንድ ሄክታር መሬት ላይ የከተማው ነዋሪ በፓርኩ በመገኘት ችግኝ በመትከል ለአርቲስቱ ያለውን ፍቅር መግለፁን አስረድተዋል ።

 በችግኝ ተከላው ከተገኙት ነዋሪዎች መካከል የዳርጌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሽመልስ ምትኩ በሰጡት አስተያየት ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ የተተከለው ችግኝ ጸድቆ ስሙ ለዘላለም እንዲጠራ ለማድረግ  አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የከተማዋ የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፍርዲሳ ገመዳ በበኩላቸው ለአርቲስቱ መታሰቢያነት በተሰየመው ፓርክ ውስጥ የተተከለውን ችግኝ ከህዝቡ ጋር በመተባበር ጸድቆ ለፍሬ እንዲበቃ ለማድረግ የሚፈለግባቸውን አስተዋፅኦ ለመወጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጅማራሬ ወረዳ በዋዩ ከተማ በዛሬው እለት ለአርቲስቱ መታሰቢያነት የችግኝ ተከላ መርሃ ግበረ መካሄዱን የወረዳው የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም