ለቴክኖሎጂና አዳዲስ ፈጠራዎች እንቅፋት የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ማስተካከል ይገባል - የዘርፉ ባለሙያዎች

72

 አዲስ አበባ  ሀምሌ 8/2012  (ኢዜአ) ኢትዮጵያን የቴክኖሎጂና የአዳዲስ ፈጠራዎች ማዕከል ለማድረግ እንቅፋት የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ማስተካከል እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

በፕላንና ልማት ኮሚሽን አዘጋጅነት ውይይት ከሚደረግባቸው 10 ዋና ዋና መሪ የልማት እቅዶች አንዱ የሆነው የቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ዛሬ ቀርቧል።

በዚህም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በዘርፉ ትደርስበታለች የተባለው እቅድ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አቅራቢነት ውይይት ተደርጎበታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ጥበበ በሻህ እንደሚሉት የአስር ዓመት መሪ እቅዱን ማሳካት ይቻላል።

የቴክኖሎጂና አዳዲስ ፈጠራዎችን በተመለከተ ያሉ ሕጎች እቅዱን ለማሳካት እንቅፋት እንዳይሆኑ ግን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለመተግበር እንደ አስፈላጊነቱ የሚያስገድዱ፣ የሚገፋፉ ወይም የሚያበረታቱ ሕጎችን መተግበር ይገባል ብለዋል።

የፌንቴክ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙኒዬር ዶሪ ለቴክኖሎጂ ዘርፉ የሚመጥኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

መንግስት የግል ኩባንያዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ ቴክኖሎጂና የፈጠራ እውቀት ባላቸው ሰዎች መመራት አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ እውቀት ላላቸው በቂ ጥበቃ አይደረግም፤ በሌላ በኩል ደግሞ እውቀት እንደ ሀብት አይቆጠርም፤ ይህ በሕግ ማዕቀፎች መስተካከል አለበት ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ 'መንግስት የወጣቶችን አቅም በመጠቀም የዘርፉን ተዋናዮች ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚቻል እምነት አለው' ብለዋል።

በቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም ያሉ ህጎችና ፖሊሲዎች ማሻሻያ ይደረግባቸዋል፤ ስራ ላይ የዋሉም አሉ ሲሉም አክለዋል።

ቴክኖሎጂ በሰው ተሰርቶ ሰዎች የሚጠቀሙበት በመሆኑ የዘርፉ ተዋናዮች በስፋት እንዲሳተፉበት እናደርጋለን ብለዋል።

የ251 ኮሙኒኬሽን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አዲስ አለማየሁ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንዲሁም ሶፍትዌር ለማበልጸግ ተዘጋጅተናል ብለን ኢንተርኔት የምናጠፋ ከሆነ አብሮን የሚሰራ አይኖርም ይህን ጎዳይ መንግስት ማየት አለበት ብለዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዓለም ዓቀፍ ቢዝነስ በመሆኑ የኢንተርኔትና የቴሌኮሙኒኬሽን ችግሮች እንዲስተካከሉ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም