ወጣቱ ኢትዮጵያን የማይመጥኑ የመከፋፈል ሐሳቦችን በማውገዝ አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል

99

ሐምሌ 8/2012  (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያን የማይመጥኑ የመከፋፈል ሐሳቦችን ሊያወግዝና አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ አስገነዘበ፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበርና የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያና ለአረንጓዴ ልማት አሻራ ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት በሚገኝ ፓርክ ችግኝ ተክለዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በአርቲስት ሃጫሉ ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው ድርጊቱ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወጣቶችን በማጋጨት የለውጡን ጉዞ ለማጨናገፍ የተሸረበ ሴራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሐሳብ ልዩነትን በሰከነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመግለጽ ለውጥ ማምጣት እንጂ መገዳደል መፍትሔ እንደማያመጣም ገልጸዋል።

በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያን የማይመጥኑ የመከፋፈል ሐሳቦችን ሊያወግዝና አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል ነው ያሉት።

የጥፋት ኃይሎች ሴራ ከስሞ የተጀመረውን የሕዳሴ ጉዞ ለማስቀጠል የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ወጣቶች አንድነት አስፈላጊ ነውም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ ገብረማርያም በበኩሉ ወጣቶቹ ችግኝ በመትከል፣ በአካባቢ ጽዳት፣ በደም ልገሳና የአረጋዊያንን ቤት በማደስ አንድነታቸውን እያሳዩ መሆኑን ገልጿል።

የወጣቶቹ አንድነት የጠላትን ድብቅ ሴራ አክሽፎ የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማስቀጠል እንደሚረዳም ተናግሯል።

የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ አቶ አመንቴ ቶላ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ወጣቶች አንድነት የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋቱን አስታውሰው፣ ወጣቱ አንድነቱን አጠናክሮ ከቀጠለ የውስጥም ሆነ የውጭ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ እንደማይሆን አክለዋል።

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆነው ወጣት ጸጋዬ እንድሪስ "አገር በሴረኞችና በወንጀለኞች ታምሳለች፤ ይህንን ሴራ ለማክሸፍ ደግሞ በአንድነት በመቆም እቅዳቸውን እንዳያሳኩ ማድረግ ያስፈልጋል" ብሏል።

"አገር የምትለወጠው የአዲስ አበባ ወጣቶች በዙሪያችን ካሉ የኦሮሚያ ወጣቶች ጋር ተኮራርፈን ሳይሆን ተቀራርበንና ተጋግዘን ስንሰራ ብቻ ነው" ያለችው ደግሞ ወጣት ቤተልሔም ከበደ ነች።

በመሆኑም "የወንድማማች ፍቅራችንን አስቀጥለን በአርቲስት ሃጫሉ ለተጀመረው የዴሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ በሠላማዊ መንገድ በመታገል የሕዳሴውን ጉዞ ለማስቀጠልም እንሰራለን" ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም