በመጪው ዘመን የገዳ ስርዓት በስርዓተ ትምህርት ተካትቶ ይሰጣል - የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ

53

ቢሾፍቱ (ኢዜአ) ሐምሌ 8 /2012  የትምህረት ጥራት ለማሳደግና የተማሪን ስነምግባር ለመመለስ እንዲረዳ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን መመስረትና የገዳን ስርዓት ያካተተ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ገለጸ። 

ቢሮው ባከናወናቸው ተግባራትና በቀጣዩ ትኩረት በሚሰጥቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በመግለጫቸው  እንዳሉት በኮቪድ 19 ምክንያት መምህራንና ተማሪዎች ቤታቸው እንዲሆኑ በተወሰነበት ጊዜም ቢሆን ቢሮው ትኩረቱን በፕሮጀክቶች መፈጸም ላይ አድርጎ አመርቂ
ውጤት አስመዝግቧል።

የትምህርቱን ማህበረሰብ ወደ እውቀት አምባ ለመመለስ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልሎች ትምህርት ቢሮዎች ጋር መምከሩን ገልፀዋል ።

በውይይቱ በተገኘው ግብዓትና በዓለም አቀፉ ተሞክሮም የኮሮና ቫይረስ የጉዳት መጠኑ እንደሚቀንስ ቢታመንም ጨርሶ መጥፋቱ ላይ ጥርጣሬ በመኖሩ ከበሽታው ጥንቃቄ እየተደረገ የመማር ማስተማር ስራውን መቀጠሉ እንደማይቀር ተናግረዋል።

በውይይቱ ስምምነት ከተደረሰባቸው ነጥቦች መካከል የተማሪ ክፍል ጥምርታን መቀነስና የትምህርት ማህበረሰብ ንጽህናውን በጠበቀ መልኩ ትምህርት ለማስቀጠል ተጨማሪ ክፍሎችን መገንባት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል ።

ለዚህ እንዲረዳም በክልሉ ብቻ 30 ሺህ ተጨማሪ ክፍሎችን ለመገንባት ታቅዶ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በክልሉ ፕሬዚዳንት በወሊሶ ስራው ተጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን አውስተዋል።


እንደ ኃላፊው ገለጻ የትምህርት ማህበረሰቡ የቅርብ ጊዜ ትኩረት በአገር አቀፍ  የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ቢሊዮን  ቸግኝ ለመትከል ከተያዘው እቅድ ውስጥ የትምህርት ዘርፉ 500 ሚሊዮን ችግኝ የሚተክል ሲሆን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ደግሞ 186 ሚሊዮን 300 ሺህ መሆኑን ተናግረዋል።


በመሆኑም መምህራንና ተማሪዎች በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይኸንን ማከናወን እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።


ዶክተር ቶላ በመግለጫቸው በቀጣዩ ዓመት ተማሪዎች ወደሚቀጥለው ክፍል ተዛውረው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑ ተማሪዎች በኮቪድ 19 እንዳይጠቁ ለመከላከልና መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል።


ተማሪዎች ቀጣዩን ክፍል ሲጀምሩ ለአንድ ወር ተኩል ያመለጣቸውን ትምህርት ከልሰው እንዲማሩ ይደረጋልም ብለዋል ።


ለአገሪቷ እንደ ትልቅ ችግር የሚነሳውን የትምህር ጥራት ለማሳደግና የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለማነጽ ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል ።


በክልሉ ብቻ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ተማሪዎች ከቤታቸው ተመላልሰው የሚማሩበትና ጤናማ የውደድር መንፈስ የሚፈጥሩበት 40 ሞዴል ትምህርት ቤቶችን መመስረትና ተማሪዎችን ወደ አገረሰባዊ እውቀቱ የሚመልሳቸውን የገዳ ስርዓት በትምህርቱ በማካተት ወደ ስራ መግባት ትልቁ ትኩረት ነው ብለዋል።


አክለውም የትምህርት ሴክተሩ ጀግናውን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ለማሰብና ተማሪዎች በእሱ ዓላማ የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት ሆኖው  እንዲታነጹ በየትምህርት ቤቶች መታሰቢያ የማኖር፣ በትውልድ ከተማው ደረጃውን የጠበቀ አዳሪ ትምህርት ቤት የመገንባትና እንደ ሴክተር የእቅሙን መዋጮ ለማበርከት እቅድ መያዙን ተናግረዋል።





  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም