ከአስር ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ኃይል የማምረት አቅምን 20 ሺህ ሜጋ ለማድረስ ታቅዷል

64

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2012 (ኢዜአ) 44 በመቶ ብቻ የኤሌክትርክ ኃይል ተጠቃሚ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኃይል ችግር ለማውጣት ከአስር ዓመት በኋላ ወደ 20 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ማቀዱን የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ።


የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ዘርፍ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የዘርፉ ሙያተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ውይይት አድርገዋል።

ዘርፉ የተፋሰስ ልማት፣ ንጹህ የመጠጥ ውኃና የመስኖ ልማት እንዲሁም የኃይል አቅርቦትን በአንድ ላይ ያየዘ ነው።

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዕቅዱን ባቀረቡበት ወቅት ''12 ዋና ተፋሰሶች ያሏት ኢትዮጵያ ከውኃ ብቻ 45 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማምረት አቅም አላት'' ብለዋል።

ከጂኦተርማል ደግሞ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላትና እስከ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም እንዳላት ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ይህን ያህል አቅም ያላት ኢትዮጵያ በ60 ዓመት ኃይል የማመንጨት ልምዷ 44 በመቶ ህዝቧን ብቻ ተጠቃሚ አድርጋለች።

''በዚሁ መሰረት በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የኃይል ማመንጨት አቅም አሁን ካለበት 4 ሺህ 413 ሜጋ ዋት ወደ 19 ሺህ 813 ያድጋል'' ብለዋል።

በዚህም የዜጎችን ህይወት ማቅለል እንደሚቻልና የኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገቱን ለማፋጠን እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በገጠርና የከተማ ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን 100 በመቶ ማድረስ፣ የገጠር የቧንቧ ውኃ ተደራሽነት ሽፋን 50 በመቶ ማድረስና ከዚሁ ዘርፍ 200 ሺህ ያህል የስራ ዕድል እንደሚፈጠርም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የተፋሰስ ልማት ስራን በስፋት ማከናወንና የተጀመረውን የመስኖ ልማት ስራ ማስፋት ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።

የተጀመሩ የኃይል ማመንጫዎችን ለማጠናቀቅ ብቻ በአስር ዓመት 106 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

የኃይል ዘርፍ አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ ''ኢትዮጵያ በተለይም በኃይል ማመንጨት በበርካታ መስፈርቶች መጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች'' ይላሉ።

በመሆኑም ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ ካልሰራች እድገቷን ማሳለጥ አትችልም ባይ ናቸው።

በግል ዘርፍ በውኃና ንጽህና ዘርፍ የተሰማሩት ኢንጂነር ጌታሁን ታገሰ በዕቅዱ ውስጥ የተካተቱት የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የሕዝብ ተሳትፎ ግዴታ መሆኑን አመልክተዋል።

ህዝቡ ተሳትፎ ካለው የተሰሩትን የልማት ፕሮጀክቶች እንደራሱ ተመልክቶት አዋጭነት ባለው መንገድ እንደሚጠቀምባቸው ገልጸዋል።

ሌላው በመስኖ ልማት ላይ ሙያዊ አስትያየቶችን የሰነዘሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ዶክተር ደረጄ ሃይሌ የመስኖ ዘርፍ ዕቅድ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ ቴክኖሎጂ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም መክረዋል።

''መስኖ ከምንም በላይ የውኃ ሃብት የሚፈልግ ዘርፍ በመሆኑ ውኃ ቆጣቢ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የተሻለ ነው'' ብለዋል።

በፕላን ኮሚሽን አስተባባሪነት በየዘርፉ እየተካሄደ ያለው የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውይይት እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም