የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ ያገኘውን አንድነት ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላትን መታገል አለበት -ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

91
አዲስ አበባ ሀምሌ 3/2010 የኦሮሞ ህዝብ  በትግል ያገኘውን አንድነት ለማበላሸት የሚጥሩ አካላትን መታገል እንዳለበት የኦህዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ። በአዳማ እየተካሄደ ባለው 8ኛው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ላይ አሁን በክልሉ ወሰንና ሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን መንስኤያቸውን በተመለከተ ከአባላቱ ጥያቄ ቀርቧል። የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ አዳነች ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ክልሉ ከሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ወሰን መነሻ በማድረግ ክልሉን ለማተራመስ ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ ብለዋል። የክልሉ ህዝብ በዚህ ወቅት ቆም ብሎ መመልከትና ጉዳዩ የወሰን ጉዳይ መሆኑን ማጤን ያስፈልጋል ነው ያሉት። በተለይ ደግሞ በቦረና እና ጉጂ አካባቢ እንዲሁም በምዕራብ ኦሮሚያ እየታየ ያለውን ሁኔታ ከኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ተቃራኒ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ወቅት በአገሪቷ ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው ምንም መሳሪያ ሳያስፈልገው መታገል እንደሚቻልም ነው የተናገሩት። ክልሉም የወሰን ጉዳይን በተመለከተ እቅድ ይዞ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። በመሆኑም የክልሉ ህዝብ አንድነቱን የማይፈልጉ  አካላት ከሚያደርጉት ድርጊት እንዲቆጠብና አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል። ኃላፊዋ አያይዘውም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ በየደረጃው ከሚገኙ ምክር ቤቶች በተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ላይ እየተወያዩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም በአዲስ አበባ የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል። ሌላው ኦሮሚኛን ተጨማሪ የፌዴራል የስራ ቋንቋ ለማድረግ ክልሉ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ወይዘሮ አዳነች። ጉዳዩ ከህገ መንግስት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ህጋዊ ሂደቶችን ተከትለው አስፈላጊዎቹ ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልጸዋል። ጨፌው በዛሬ ውሎው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አፈጻጸምና የክልሉ ዋና ኦዲተር ክንውን ላይም ውይይት ያደርጋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም