በሲሚንቶ ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ቢሰራም ውጤት አልተገኘም--- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር

109

አዲስ አበባ ሀምሌ 7/2012 (ኢዜአ) የሲሚንቶ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ችግርን ለመፍታት እየተሰራ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ውጤት አለመገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴር አስታወቀ። 
የኢንዱስትሪ ሚንስቴር  የሲሚንቶ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሰራ ያለውን ሥራ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩም በሚኒስቴሩ የተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀረበ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የሚስተዋለውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ቀደም ሲል ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዚህም አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ላይ ያለውን ክፍተት በመለየት እንዴት መስራት እንዳለባቸው እና የመንግስት የቁጥጥር ሥራው ምን መልክ መያዝ እንዳለበት በሚኒስቴሩ በኩል በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በእዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በጊዜው ለማቅረብ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደተግባር ተገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሰራር ከመዘርጋት በተጨማሪም የማበረታታት ስራ እየተሰራ መሆኑንም የጠቆሙት አቶ መላኩ፣ ፍላጎትና አቅርቦትን የማጣጣምና የቁጥጥር ሥራ መከናወኑንም አክለዋል።

ይሁንና ችግሩ እንዲፈታ እነዚህ ሥራዎች ቢሰሩም በሚፈለገው ልክ ውጤት አለመገኘቱን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።  

"በአሁኑ ወቅትም በሲሚንቶ አቅርቦት በኩል ክፍተት አለ" ያሉት አቶ መላኩ፣ ክፍተቱ በአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶችና ቸርቻሪዎች ላይ እንደሚስተዋል አስረድተዋል።

ችግሩ ጊዜ የማይሰጠውና መስተካከል ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ክፍተቱን በዘላቂነት ለማረም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኑረዲን መሀመድ በበኩላቸው በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ የሲሚንቶ ዋጋን ለማረጋጋት በስርጭት ውስጥ ያሉትን ተዋንያን በሙሉ ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲገቡ መዋቅር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

በዚህም አምስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ 67 አከፋፋዮች እንዲሁም 12 ፋብሪካዎች በትስስር ውስጥ እንዲገቡና የእለት ተእለት የምርት፣ የስርጭት፣ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታዎች ላይ ክትትል ሲደረግ እንደነበረ ነው የገለጹት።

በእዚህም ከፍተኛ የሲሚንቶ የማከፋፋያ ዋጋን በማስቀመጥ ምርቱ በመንግስት በተቀመጠውና ከእዚያ በታች በሆነ ዋጋ እንዲሸጥ የማድረግ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አከበረኝ ወጋገን በበኩላቸው በርካታ ግለሰቦች በሲምንቶ እጥረት ምክንያት የግንባታ ሥራቸውን አቋርጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የሲሚንቶ አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በበኩላቸው ኮሚቴው በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ተግባራት ጥሩ ቢሆኑም በቀጣይ ብዙ ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም