ኮርፖሬሽኑ በመዲናዋ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግንባታ እያከናወነ ነው

70

አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 7/2012 (ኢዜአ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመዲናዋ በአምስት ሳይቶች የጀመራቸው የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግንባታ በሁለት ዓመት እንደሚጠናቀቁ ተገለጸ። 


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኮርፖሬሽኑን የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

አባላቱ ኮርፖሬሽኑ ከ28 ዓመታት በኋላ ያስጀመራቸውን የመኖሪያ፣ የንግድ ቤቶችና የዋና መስሪያ ቤት ህንጻዎች የግንባታ ሂደትም ተመልክተዋል።

የኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል የተቋሙን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ሲያብራሩ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦች እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የተቋሙን ጠቅላላ ንብረት የማደስ፣ የመቁጠርና የመመዝገብ ስራ መከናወኑንና የኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ንብረትም 71 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ ማወቅ እንደተቻለም አስረድተዋል።

የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማቃለል ከ28 ዓመታት በኋላ በመዲናዋ ቁልፍ ቦታዎች ላይ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

የቤቶቹ ግንባታ በሁለት ምዕራፍ እንደሚከናወንና በመጀመሪያ ምዕራፍም በአምስት ሳይቶች የግንባታ ስራ መጀመሩንና በሁለት ዓመት እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ሊገነባቸው ላቀዳቸው ከ15 ሺህ በላይ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም አቶ ረሻድ አስታውቀዋል።

የቤቶቹ ግንባታ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት ይከናወናልም ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ ተቋሙ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ በቤቶች ግንባታ፣ የራሱን ገቢ በማመንጨትና በሌሎችም ተግባራቱ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ የኅብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለሟሟላት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ኮሚቴው  አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ተማግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ በመዲናዋ ዘመናዊ መንደር የመገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም