ሁከት በመፍጠር የተጠረጠሩት አቶ በቀለ ገርባ ላይ መርማሪ ፖሊስ ላቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 9 ተቀጠረ

60

አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 7/2012 (ኢዜአ) ሁከት በመፍጠር የተጠረጠሩት አቶ በቀለ ገርባ ላይ መርማሪ ፖሊስ ላቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ  ለሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ተቀጠረ። 

በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩት እነ ደስታ ቶሎሳ ላይ በተመሳሳይ ዕለት ትዕዛዝ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መርማሪ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ ያከናወናቸውን ስራዎች በዝርዝር አቅርቧል።

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የአራዳ ተረኛ ወንጀል ችሎት ላይ መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው መሰረት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን አስከሬን ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ይዞ ለመግባት በተደረገ ሙከራ በወቅቱ የተገደለው የጥበቃ አባል በጥይት ስለመገደሉ በህክምና ማስረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።

በተጨማሪም የ26 ምስክሮችና የ31 ተጠርጣሪዎችን ቃል መስማቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የተፈጠረውን ሁከት ተከትሎ የደረሰውን የንብረት ውድመት በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ያመለከተው መርማሪ ፖሊስ ሁለት ተቋማት ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት እንደወደመባቸው የገለጹለት መሆኑን አስረድቷል።

ሌሎች ድርጅቶችም የደረሰባቸውን ጉዳት እንዲያሳውቁት በደብዳቤ ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል።

በወንጀል ድርጊት የጠረጠራቸው አቶ በቀለ ገርባ ስልክ በመደወል ሁከት እንዳነሳሱ ገልጾ፤ በዚህ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ሰባት የመርማሪ ቡድን ወደ ክልል ተሰማርቶ የማጣራት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

በተጨማሪም ከተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት ሁለት ሽጉጥ ማግኘቱን ገልጾ፤ መሳሪያው ፈቃድ ያለው ስለመሆኑ እንዲሁም ወንጀል የተፈጸመበት ስለመሆኑ ለፎረንሲክ ምርመራ በመላክ ውጤቱን እየተጠባበቀ እንደሆነ አመልክቷል።

አቶ በቀለ ገርባ የተጠረጠሩበት ወንጀል ውስብስብና ተጨማሪ ማጣራት የሚፈልግ በመሆኑም 14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው አቶ በቀለ ገርባ ምንም ስልክ እንዳልደወሉ በመናገር ወንጀል እንዳልፈጸሙ ገልጸው፤ መኪናቸው በመታሰሯ ቤተሰብ ለመንቀሳቀስ መቸገሩን ተናግረዋል።

ከቤታቸው ሁለት ሽጉጥ መገኘቱ ትክክለኛ መሆኑን በመግለጽ፤ አንደኛው ሽጉጥ ፈቃድ ያለውና የማይሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ሁለተኛው ሽጉጥ ደግሞ የማይሰራውን ባለፈቃድ ሽጉጥ በመመለስ ፈቃድ ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ አስረድተዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ደንበኞቻቸው ቤተሰብና ጠበቃ እንዳያያቸው መደረጉንና ሚዲያ ዘመቻ እያካሄደባቸው መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

ጠበቆቹ ደንበኛቸውን ለአንድ ቀን ብቻ እንዳገኙ የተናገሩ ሲሆን፤ በተጨማሪም የደንበኛቸው የወንጀል ድርሻ ተለይቶ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪውና በጠበቆች ለቀረበው ጉዳይ በሰጠው ማብራሪያ የተጠርጣሪው መኪና በወንጀል ፍሬ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ገልጿል። ተጠርጣሪው በግል ስልካቸው ደውለው አመጽ ተቀጣጥሎ እንዲቀጥል መልዕክት ማስተላለፋቸውን የሚገልጽ ማስረጃ እንዳለውም አመልክቷል።

የቤተሰብ ጥየቃን በተመለከተም ወቅቱ የኮሮናቫይረስ ስጋት ያለበት በመሆኑ የተወሰኑ ቤተሰቦች ብቻ እንዲጠይቁ የተፈቀደ መሆኑን በማስረዳት ጠበቆችም እንዲያገኟቸው እየተደረገ መሆኑን ገልጿል፤ በዚህ ረገድ የሚታይ ክፍተት ካለ እንደሚስተካከል ገልጿል።

የተጠርጣሪው የወንጀል ድርሻ ተለይቶ ይቅረብ ለሚለውም ወንጀሉ ውስብስብና የቡድን ስምምነት ያለበት በመሆኑ ተለይቶ መቅረብ አስቸጋሪ እንሚሆን መርማሪ ፖሊስ አስረድቷል። 

ግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው የቀረቡት እነ ደስታ ቶሎሳ ላይ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ማጣራት ለማድረግ የ14 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የጠረጠራቸው እነ ደስታ ቶሎሳ ላይ 26 ምስክር እና 31 ተጠርጣሪዎች ቃል መስማቱን ገልጿል።


በተፈጠረው ሁከት የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ለተቋማት ደብዳቤ ጽፎ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን፣ በክልል የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ሰባት መርማሪ ቡድን መላኩን፣ የጦር መሳሪያዎች ወንጀል የተፈጸመባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ለፎረንሲክ ምርመራ መላኩን፣ ተጨማሪ የህክምና የሰውና የሰነድ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ እንደሚቀረው በመግለጽ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ምን ያህል ምስክር መስማት እንደሚቀረው፣ የእያንዳንዱ የደንበኞቻቸው የወንጀል ድርሻ በዝርዝር እንዲቀርብ፣ ታስረው የሚገኙበት ቦታ ቤተሰብ እንዲጠይቃቸውና ከጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲደረግ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ እንደገለጸው፤ ለተፈጸመው የወንጀል ድርጊት የሚያስፈልጋቸውን የምስክር መጠን መግለጽ አዳጋች ነው።

የወንጀሉ ሁኔታ ውስብስብ በመሆኑና በቡድን ስምምነት የተፈጸመ በመሆኑ ለእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ለይቶ ማቅረብ እንደማይቻል ገልጿል።

ተጠርጣሪዎችን ለማግኘት ምንም የጠበቃ ጥያቄ አለመቅረቡን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በስፋት የቤተሰብ ጥየቃ አለመኖሩን አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎች የታሰሩበትን ቦታ በችሎቱ ላይ ለጠበቆች አሳውቋል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ለተጠየቀው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም