በህዳሴ ግድብ ዙሪያ መገናኛ ብዙሃን የህዝቡን ተሳትፎና አንድነት ለዓለም ማሳየት እንዳለባቸው ተመለከተ

73

ሐምሌ 6/2012 (ኢዜአ ) በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና በብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ይልቅ ሃገራዊ አንድነትን አስቀድመው ሊሰሩ እንደሚገባ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ጌታቸው ጥላሁን ገለጹ።

የጋዜጠኝነት የሙያው ስነ-ምግባር ከአድሏዊነትና ወገንተኛነት በራቀ መልኩ ህዝብና ሃገርን ማገልገልን፣ ለእውነት መመስከርን እንደሚጠይቅም ምሁሩ ተናግረዋል። 
 
ዶክተር ጌታቸው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ እንደገለጹት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅና ፍትሓዊ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚነት መረጋገጥ የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
 
ይሄ የግንባታ ፕሮጀክት ለውጤት እንዲበቃ ማንንም ሳይጎዳ በእኩል ተጠቃሚነት መርህ መሰረት በህዝቡ ሀብት እየተገነባ እንደመሆኑ ህዝብን ከማስተባበር ባለፈ ድምጹን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የማሰማት ኃላፊነትም ከመገናኛ ብዙሃኑ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
 
“የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጫፍ የደረሰ የሃገራዊ ጥቅምና ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ሆኗል” ያሉት ምሁሩ “በዚህ ዙሪያ ከሌላ ወገን ጋር ሊንቀሳቀስ የሚችል ሚዲያ የኢትዮጵያ ሚዲያ አይደለም” ብለዋል
 
የሃገር ጉዳይን ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር አደባልቆ መሔድ ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸው፤ሃገር ከሌለ ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል በመረዳት ለጉዳዩ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስረድተዋል።
 
ፖለቲካው የሚኖረው የራስን ሃሳብም እንደፈለገ መግለጽ የሚቻለው ቅድሚያ የተረጋጋ ሃገር ሲኖር በመሆኑ መገናኛ ብዙሃኑ ከፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነት ይልቅ በብሔራዊ ጥቅም ላይ በጥንቃቄ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
 
ከዚህ ባለፈ የጋዜጠኝነት የሚድያ ስነ-ምግባር ከአድሏዊነትና ወገንተኛነት በራቀ መልኩ ህዝብና ሃገርን ማገልገልን ለእውነት መመስከርን እንደሚጠይቅ ጠቁመው ከዚህ አኳያ በየጊዜው በተለያየ መልክ የሚገለጽ ሰፊ ውስንነት እንደሚስተዋል ተናገረዋል።
 
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር መገናኛ ብዙሃኑ የቅስቀሳ መሳሪያ ሆነው የሚያገለግሉበት ሁኔታ እንደነበረ አስታውሰው አሁን ላይ ብዝሃ አስተሳሰብ በነጻነት የሚንሸራሸርበት እድል ቢመጣም በበቂ ደረጃ እንዳልተሰራበት ገልጸዋል።
 
የተወሰኑ አካላትን የተለያዩ ፍላጎቶች ማሟላት እስካልተቻለ ድረስ የሃገርን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል የዘገባ ስራ ላይ የመወሰድ ሁኔታ በግልጽ እየታየ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
 
“ሃገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ አለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ዘልቆ ሊገባ የሚችል ጠንካራ መገናኛ ብዙሃን የሉንም” ያሉት ዶክተር ጌታቸው በዚህ የተነሳም የህዝቡን ፍላጎትና ድምጽ በበቂ ሁኔታ ማሰማት እንደማይቻል ተናግረዋል።
 
በቀጣይም ይሄንን ሊሰራ የሚችል ሚዲያ ለመፍጠር መንግስት ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት በመጠቆም ጋዜጠኞችም እራሳቸውን ለወቅታዊው ሁኔታ ብቁ በማድረግ በኃላፊነት የመስራት ልምዱ ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
 
የሃገርን ደህንነት የሚጎና እንዲሁም ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ የዘገባ ስራ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል እንደመሆኑ ቀጥተኛ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና ክትትል የሚያስፈልግ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም