በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች ማህበረሰቡና መንግስት እንዲያቋቁሟቸው ጠየቁ

109

አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2012 (ኢዜአ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሰበብ በማድረግ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ሀብትና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች ማህበረሰቡና መንግስት እንዲያቋቁሟቸው ጥሪ አቀረቡ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የግርግሩ ተጎጂ የሻሸመኔ፣ ባቱና አርሲ ነገሌ ከተሞች ነዋሪዎች ለዓመታት ወልደው ከብደው በኖሩበት አካባቢ በሰዓታት ልዩነት ሀብት ንብረታቸው በሙሉ እንደወደመባቸው ገልጸዋል።

ሰኔ 22 ቀን 2012 ምሽት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በአዲስ አበባ መገደሉን ተከትሎ ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ በተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ወደከተማ መግባቱን ነዋሪዎቹ ያስታውሳሉ።

ከዚያም ከንጋት ጀምሮ በርካታ ወጣቶች ወደ ንብረት ማውደም ተግባራት መሰማራታቸውን ይገልጻሉ።

ወጣቶቹ ወደ ንብረት ማውደም ተግባር የገቡበትን ምክንያት ነዋሪዎች እንዳላወቁትም አመልክተዋል።

በዚህም የመኖሪያና የንግድ ቤትና ንብረታቸው እንዲሁም ተሽከርካሪ፣ አልባሳትና ሰነዶች ሳይቀር እንደተቃጠለባቸው ጠቁመዋል።

ከደርግ ዘመን ጀምሮ በሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ መሆናችውን የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ አለሙ ከአካባቢው ማህበረሰብ በጋብቻና በማህበራዊ ህይወት ተሳስረው ለፍተው ያፈሩት ሀብት መና መቅረቱን ተናግረዋል።

የባቱ ከተማ ነዋሪው አቶ ሞላ ይታየው በበኩላችው ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ከልጅነት እስከ እውቀት ከትንሽ ሱቅ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱባቸው ሆቴሎች፣ ሱቆችና መኖሪያ ቤት ወድመውባቸዋል።

በተመሳሳይ የባቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሰብለ ዋሴ፣ አቶ ስማቸው ዓለሙ እንዲሁም የአርሲ ነገሌ ከተማ ነዋሪው አቶ ዮናስ ሰርጎብርሃን ከሰኔ 23 ጀምሮ በተፈጠረው ግርግር ሀብት ንብረታቸው ወድሞባቸው ሰው ተጠግተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በከተሞቹ በኖሩባቸው ዓመታት ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በሰላምና በፍቅር መኖራቸውን የሚናገሩት ተጎጂዎቹ፤ 'የሰሞኑ ሁኔታ ይከሰታል' በሚል ስጋት አድሮባቸው እንደማያውቅ ተናግረዋል።

በከተሞች በሚደረጉ ማህበሰረባዊ በጎ አድራጎት ተግባራትም ሲሳተፉ ራሳቸውን እንደባዕድ ቆጥረው እንደያማውቁም ተናግረዋል።

በጥፋቱ የተሳተፉ ወጣቶችንም የማያውቋቸው እንደሆኑ ገልጸው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች መጠጊያ ከመስጠት ጀምሮ እሳቱን ለማጥፋትና ንብረቱን ከጥፋት ለመታደግ ጥረት ቢያደርጉም ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ማዳን እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

የነበራቸውን ሃብት አጥተው ባዶ መቅረታቸውን ገልጸው፤ ማህበረሰቡና መንግስትም ደግፈው እንዲያቋቁሟቸው ጠይቀዋል።

መንግስት ህጋዊ ከላላ እንዲሰጣቸውና በአጥፊዎች ላይም የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ተማጽነዋል።

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ደበል በበኩላቸው በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው ድርጊቱ ከባህልና ልማድ ያፈነገጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በወቅቱ ጥፋቱን የፈጠሩ ሰዎች ከየት እንደመጡ የማይታወቁና በጣም ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው መሆኑ ከነዋሪ አቅም በላይ በመሆኑ ጥፋቱን መከላከል እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

የአካባቢው ሰው በተቻለ መጣን የሰው ህይወት ለማዳን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም