የሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ከ74 በመቶ በላይ አገግሙ

57

አዲስ አበባ  ሀምሌ 6/2012 (ኢዜአ) በሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ከሚገኙ የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ከ74 በመቶ በላይ አገግመው ማህበረሰቡን መቀላቀላቸው ተገለጸ።

በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ 304 ሕሙማን ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸው ታውቋል።


ለሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ሕክምና ማዕከል ድጋፍ ላደረጉ አካላት የእውቅና ተሰጠቷል።

ማዕከሉ የኮሮናቫይረስ ሕሙማን መቀበል ከጀመረ ዛሬ 40 ቀናትን አስቆጥሯል።

ማዕከሉ የኮቪድ-19 ሕክምና አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት ለሁለት ወራት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የማዕከሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ ገልጸዋል።

እስካሁን ማዕከሉ 1 ሺህ 417 ሕሙማን መቀበሉንና ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 58ቱ ወይንም 74 ነጥብ 6 ከመቶው ከቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ አገግመው ወደማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል።

"ለወሊድ አገልግሎት፣ ለቆዶ ሕክምናና ለተጓዳኝ በሽታዎች ሕክምና የመጡ 55 ሕሙማን በማዕከሉ የኮቪድ-19 ሕክምና ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ ወደ ሌሎች የጤና ተቋማት እንዲላኩ ተደርገዋል" ብለዋል።

ዶክተር ውለታው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ 304 ሕሙማን ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

የቆሻሻ አወጋገድ ስርአት መዘርጋት፣ የጤና ባለሙያዎችን ወደ ስራው ማስገባት፣ የግዢ ስርአቱ ለአስቿኳይ የህክምና ግብአቶች ግዢ ምቹ አለመሆንና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች አለመሟላት ማዕከሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ከጀመረ በኋላ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮቹ እንዲፈቱ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሰራቱንም ጠቁመዋል።

ማዕከሉ አሁንም ለኮሮናቫይረስ ሕሙማን አስፈላጊውን ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ለማዕከሉ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ዶክተር ውለታው ምስጋና አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በማዕከሉ የተሰራው ሥራ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ወደፊት መሻገር እንደምትችል የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይም ብዙ የቤት ሥራ የሚጠበቅ በመሆኑ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

"ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እየሰሩ ላሉ የሕክምና ባለሙያዎች ትልቅ ክብር ይገባቸዋል" ብለዋል ዶክተር ሊያ።

የዓለም የጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የድንገተኛ ሕክምና ኦፊሰር ዶክተር አማረ ወርቅዬ ድርጅቱ ለማዕከሉ ያደረገው ድጋፍ ቆሻሻ ማስወገድ የሚያስችል መሳሪያ እንደሆነ ገልጸዋል። በድርጅቱ በኩል ለማዕከሉ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም