ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በታዋቂው ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለፁ

207

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በታዋቂው ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዘን መግለጫቸው “ውድ ህይወት አጥተናል” ብለዋል።

“የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳ ህይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁም” ነው ያሉት።

የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የድርጊቱን መጠን በመረዳት በሀገራችን ውስጥ ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች ትኩረት ሰጥተን የምንከታተልበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ሀዘናችንን ራሳችንን በመጠበቅ እና ተጨማሪ ወንጀልን በመከላከል እንግለፅ ሲሉም አሳስበዋል።

አርቲስቱ ምሽት ላይ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለኢቢሲ እንደተናገሩት የከተማዋ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ግድያውን በመፈፀም የተጠረጠሩ የተወሰኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሏል።