በ24 ሰዓታት ምርመራ ተጨማሪ 157 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው፤ የ5 ሰዎችም ሕይወት አልፏል

54

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3 ሺህ 693 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 157 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸውና የ5 ሰዎች ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 846 ደርሷል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው 132 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 5 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 5 ሰዎች ድሬደዋ ከተማ አስተዳዳር ፣ 5 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 3 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 3 ሰዎች ከሶማሊ ክልል፣ 3 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልልና 1 ሰው ከቤንሻነንጉል ጉሙዝ ክልል ናቸው፡፡

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 97 ወንዶችና 60 ሴቶች ሲሆኑ 156 ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ 1ቱ የውጭ አገር ዜጋ ነው፡፡

ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከ7 እስከ 83 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙም ተጠቅሷል፡፡

ከሟቾች መካከል 4ቱ በአስከሬን ላይ የተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ ሲሆን 1 ሰው በህክምና ማዕከል በህክምና ላይ እያለ ህይወቱ አልፏል፡፡   

በዚህም ባለፉት 24 ሰዓታት በድምሩ የ5 ሰዎች ህይት አልፏል፡፡

በአጠቃላይ በሃገራችን ቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 103 መድረሱ ተገልጿል፡፡  

የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዜጎች ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተዋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው ዕለት 200 ከአዲስ አበባ፣ 87 ከሶማሌ ክልል፣ 9 ከአማራ ክልል፣ 1 ከኦሮሚያ ክልልና 1 ከድሬዳዋ) በድምሩ 298 ሰዎች ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ በአገራችን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 2 ሺህ 430 ደርሷል፡፡  

በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ 3 ሺህ 311 ሰዎች ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 35 በፅኑ ህሙማን ክፍል ያሉ ናቸው።

በኢትዮጵያ እስካሁን 250 ሺህ 604 የላቦራቶሪ ምርመራ መካሄዱም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም