ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በአማካይ 10 ነጥብ 2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚኖራት ተገምቷል

157

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት በአማካይ 10 ነጥብ 2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ልታስመዘግብ እንደምትችል የፕላንና ልማት ኮሚሽን ገለጸ።

የፕላንና ልማት ኮሚሽን የኢትዮጵያን የ10 ዓመታት ጉዞ መልክ ያስይዛል ያለውን ብሔራዊ እቅዱ ላይ ውይይት ማድረግ ጀምሯል።

የልማት ዕቅዱ ከ2013 እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር ሲሆን 'ኢትዮጵያ፣ አፍሪካዊ የብልጽግና ተምሳሌት' የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በዛሬው ውይይት ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ እንደገለጹት ረቂቅ መሪ እቅዱ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግር ነው።

ዕቅዱ ለየት ያለ መሆኑን የሚናገሩት ኮሚሽነሯ ዘርፎች በጋራ ሆነው ያዘጋጁት፣ የብዝሃ ዘርፍ ልማት ላይ ያተኮረ፣ የመልማት አቅምና እምቅ አቅም ላይ ያተኮረና በልዩ ሁኔታ ክትትልና ግምገማ የሚደረግበት ነው ብለዋል።

መሪ እቅዱ ጥራት ያለው እቅድ ማረጋገጥ፣ ምርታማነትን ማሳደግ፣ የዘርፎችን ትስስር ማጠናከር፣ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ማሳተፍና የሴቶችና ሕጻናት እኩል ተሳትፎ እንዲሁም አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባትን ምሰሶ ያደረገ ነው ብለዋል።

በነዚህ መነሻዎች ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት አማካይ አመታዊ እድገቷ 10 ነጥብ 2 በመቶ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል።

በእድገቱ ግብርና 6 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 13 በመቶና የአገልግሎት ዘርፉ 10 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሏል።

በመሪ እቅዱ መሰረት የዜጎች አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ8 ነጥብ 2 በመቶ የሚያድግ ሲሆን በአስር ዓመቱ መጨረሻ ላይ የአንድ ኢትዮጵያዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ 2 ሺህ 248 ዶላር እንደሚሆንም ተገምቷል።

ከአስር ዓመት በኃላ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ኢትዮጵያን ቁጥር ወደ 7 በመቶ ዝቅ እንደሚልና የከተማ ስራ አጥነት ምጣኔም 9 በመቶ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክ አቅርቦት ረገድም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚሆንና ብሔራዊ ኃይል የማመንጨት አቅምም 21 ነጥብ 1 ጊጋ ባይት ይደርሳል ተብሏል።

በመሪ እቅዱ መሰረት የግብርና ሚና እየቀነሰ ሄዶ ትልቁን ስፍራ የሚይዘው የኢንዳስትሪ ዘርፍ ይሆናልም ተብሏል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር ታደለ ፈረደ እንዳሉት መሪ አቅዱ ዋና ዋና አቅጣጫዎችን በሚያመለክት መልኩ የተዘጋጀ ነው።

መሪ እቅዱ በተለይም ጥራት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥና ፍትሃዊ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።

ይህም ሲባል ድህነትን መቀነስ መቻል፣ ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ፣ ቀልጣፋ አሰራርና አስተዳደር መዘርጋትና በጥቅሉ ለዜጎች የተመቸ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

እቅዱ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ሁኔታዎችን የሚያመቻችና የአገር ውስጥ አምራቾችን የሚያግዝ መሆን አለበትም ብለዋል።

የግብርና ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዶክተር ጌታቸው ዲሪባ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ እቅዱ አሳታፊ ኢኮኖሚ መገንባት መቻል አለበት ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በቀጣዮቹ አስር ዓመታት 22 ሚሊዮን ሰው ጨምሮ ፍላጎቱ ከባድ ይሆናልም ብለዋል።

በመሆኑም ምርታማነት በቅልጥፍና እና በፍጥነት ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ነው ያሉት።

ከምንም በላይ ደግሞ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ቴክኖሎጂን መጠቀም መቻልና የዘርፎች እርስበርስ ትስስር በእቅዱ ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

እቅዱ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊታገዝ እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ የዓለም ባንክ አማካሪዋ ወይዘሪት ፋንቱ ፋሪስ ናቸው።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የግሉ ዘርፍ የካፒታልና የቴክኖሎጂ ውስንነት፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግርና የተወሳሰበ የመንግስት ቢሮክራሲ እየፈተነው ነው ብለዋል።

በመሆኑም መሪ እቅዱ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጎለብት መሰል ችግሮችን ማስወገድ የሚችሉ መንገዶችን ቢዘረጋ መልካም መሆኑን መክረዋል።

በውይይቱ ወቅት ለምን የአስር ዓመት እቅድ ማዘጋጀት አስፈለገ? እውን በአስር ዓመት ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል ወይ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል።

እቅዶች ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ቢታቀዱ መልካም መሆኑንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ መንገድ የሚጠርግ መሆኑ ተብራርቷል።

በመሪ እቅዱ ላይ ለቀጣዮቹ አስር ቀናት ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ግብዓት ይሰበሰባልም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም