በትግራይ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን በ4እጥፍ ብልጫ እንዳለው ተገለጸ

705

ሽሬ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) ከትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በባሕላዊ መንገድ ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ መጨመሩን የዞኑ ማዕድንና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የማዕድንና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ካልአዩ ብርሃነ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በባሕላዊ መንገድ ተመርቶ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሽሬ ቅርንጫፍ የቀረበው የወርቅ መጠን ከአምስት ስድስት ኩንታል ነው።

ዘንድሮ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ከአምና ጋር ሲነጻጸር በአራት ኩንታል ብልጫ አለው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ከክልሉ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን አንድ ነጥብ አራት ኩንታል ወርቅ ብቻ እንደነበር አስተባባሪው ተናግረዋል።

ለባንኩ የቀረበው የወርቅ መጠን በአራት እጥፍ ሊጨምር የቻለው ሕገወጥ ወርቅ አዘዋዋሪዎችን በተቀናጀ ቁጥጥር ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በመደረጉ ነው።

ብሔራዊ ባንኩ ለምርቱ አቅራቢዎች 20 በመቶ የማነቃቂያ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉም ለምርቱ መጨመር አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ከ150 ግራም በታች ወርቅ ከአምራቾች እንዳይቀበል ይከለክል የነበረው የብሔራዊ ባንክ መመሪያ በመሻሻሉም የቀረበው የወርቅ መጠን እንዲጨምር አድርጓል።

የባንኩ አሰራር በአሁኑ ጊዜ ተሻሽሎ ከ50 ግራም አንስቶ መቀበል በመጀመሩ ወደ ባንኩ የሚቀርበው በባሕላዊ መንገድ የተመረተ የወርቅ ምርት እንዲጨምር ማገዙን አቶ ካልአዩ ተናግረዋል።

በዞኑ በባሕላዊ መንገድ ወርቅ በሚመረትባቸው አምስት ወረዳዎች በ156 ማኅበራት የተደራጁ 2 ሺህ 856 ዜጎች ወርቅ በማምረት ላይ ይገኛሉ።

ወደ ብሔራዊ ባንኩ ዘንድሮ የቀረበው ወርቅ በወቅታዊ የገበያ ዋጋ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መሆኑን የዞኑ ማዕድንና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።

በብሔራዊ ባንክ የሽሬ ቅርንጫፍ ተወካይ ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው የቀረበው የወርቅ መጠን ትክክለኛ መሆኑን ጠቅሰው ዝርዝር መረጃ ለመናገር ግን ከመሥሪያ ቤታቸው ኃላፊነት እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

ከባሕላዊ ወርቅ አምራቾች መካከል አቶ ልዑል አብርሃ በሰጡት አስተያየት ብሔራዊ ባንኩ ከአሁን በፊት ከ150 ግራም በታች ወርቅ ስለማይቀበል የተጠቀሰውን ወርቅ ለማጠራቀም ረጅም ጊዜ መጠበቅ ግድ ይል ነበር ብለዋል።

አሁን ግን ብሔራዊ ባንኩ ዝቅተኛ የአቅርቦት መጠን 50 ግራም በማድረጉ በእጃችን ያለውን ወርቅ እንድናቀርብ አግዞናል ብለዋል።

ብሔራዊ ባንኩ ለሕጋዊ ወርቅ አቅራቢዎች ማነቃቂያ 20 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ለአቅርቦቱ መሻሻል አስተዋጽኦ ማበርከቱን የተናገሩት ደግሞ በዘርፉ የተሰማሩት አቶ አበጋዝ ብርሃነ ናቸው።