ጃፓን በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ለመከላከል የሚውል 4 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች

62

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) የጃፓን መንግስት ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያደረሰውን ተፅእኖ ለመከላከል ለሚያከናውነው ተግባር የሚውል 4 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች።

ዓለም አቀፍ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅእኖ ለመከላከል ለሚያከናውነው የአስቸኳይ ጊዜ እገዛ የሚውል የጃፓን መንግስት 4 ሚሊዮን ዶላር መለገሱን የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት አስታውቋል።

ድጋፉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዙ የኢንፌክሽን መከላከያ፣ ህይወት አድን የመጠጥ ውሃና የጤና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት፣ የጤና አጠባበቅ ግንዛቤ ማሳደግ የሚውል ነው።

በተጨማሪም 8 ሺህ ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች አቅም ለመገንባትና 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች የኮሮናቫይረስን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እገዛ ያደርጋል ተብሏል።

በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ አዴል ኮደር “ከጃፓን ያገኘነው እገዛ በአስፈላጊ ጊዜ የደረሰ ነው፤ መንግስት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በህፃናትና ችግር ባጠቃቸው ቤተሰቦች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል" ብለዋል።

የጃፓን መንግስት ያደረገው ድጋፍ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ 750 ሺህ ለሚሆኑ ህፃናትና ሴቶች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና እና ንፅህና አጠባበቅ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ  የሚከናወነውን ጥረት ያግዘዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም