ከግብፅ ሴራ ጀርባ ያሉ ኃይሎች እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጠየቁ

108

ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) በአባይ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ሴራ ጀርባ በመሆን የሚንቀሳቀሱ የውጪ ሆነ የውስጥ ኃይሎች እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት አሳሰቡ።

የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በአባይ ጉዳይ አንዳንድ የውጪና የውስጥ ኃይሎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ትክክል ያልሆነና በየትኛውም መመዘኛ ያልተገባ ነው።

የማህበር አባል የሆኑት አቶ ደስታ አርቤሎ፣ የሀገር ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው፤ አንዳንድ የውጪና የውስጥ ኃይሎች አባይን በተመለከተ የሚያራምዱት አቋም ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

የትናንት ጀግኖች በጦር ሜዳ በብዙ መስዋዕትነት ያቆዩልን ሀገራችን ስትነካ ያማል ያሉት አርበኛው ፣ ይህ ህመም የትኛውንም ዋጋ ለሀገር ለመክፈል አቅም የሚፈጥር እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሁሌም ኢትዮጵያ ለመልማት ስትንቀሳቀስ የውጭ ኃይሎች የልማቱ አደናቃፊ ሆነው እንደሚቆሙ አመልክተው፣ "ግብፆች እነሱ እየለሙ እኛ በድህነት እንድንኖር ሊፈርዱብን አይገባምም፤ ለዚህ የሚሆን አቅምም ሥልጣንም የላቸውም" ብለዋል።

አባላቱ አክለውም "ግብጽ የተለያዩ የውጪ ኃይሎችን ጨምሮ ከውስጥ ኃይሎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች፤ አሁንም እያከናወነች ትገኛለች " ሲሉ ገልጸዋል።

ከግብጽ ሴራ በስተጀርባ ውስጣዊ ጠላት አለ የሚሉት አርበኛ መሪጌታ አምዴ ወልደ ጻድቅ ፤ "ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነው። አስቀድሞ መጠንቀቅ የውስጥ ጠላትን ነው" ብለዋል።

እኛ በሰላም የምትኖር ሀገር እየተመኘን ነው ያሉት አርበኛ መሪጌታ አምዴ፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ስልጣን ለኛ ካልደረሰን ሀገሪቷ መበታተን አለባት በማለት ሕዝባችንን በቋንቋ፤ ኃይማኖትና በዘር እየከፋፈሉ ሀገሪቱን ወደ አልተገባ መንገድ የሚወስዱ ኃይሎች ከዚህ ካልተገባ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም