ለብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም ጉባኤ የቅድመ ዝግጅት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

112
አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2010 በብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም ጉባኤ በቅድመ ዝግጅት ሂደት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት አለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥሪ አደረገ። ኮሚቴው በየካቲት ወር በአሜሪካ በተካሄደ ጉባኤ መሰረት ስድስት በውጭ የሚኖሩና አምስት አገር ውስጥ በሚሰሩ ፓርቲዎች በተውጣጡ አባላት የተቋቋመ ነው። ኮሚቴው ''የአገራችንን ወቅታዊ ችግሮችና መፃኢ እድሎችን ለመወሰን ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ብቸኛ አማራጭ ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ በመጪው ነሐሴ ወር ጉባኤ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ መሆኑን ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደኃላፊነት ከመጡ ወዲህ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን መሆን የይቅርታ፣ የመፈቃቀር፣ የመግባባትና የአንድነት ህዝባዊ ጥሪ የሚበረታታ እንደሆነ ኮሚቴው አስገንዝቧል። በመሆኑም በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ በብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ላይ ፅኑ እምነት ያላቸው አካላት በጋራ በመሆን ጉባኤውን በአዲስ አበባ ከተማ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅቱ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል። ጉባኤው በአገሪቱ የፖለቲካ ጥላቻን በማስቀረት የተረጋጋችና ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ አገር ለመገንባትና ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ለመፍጠር ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተጠቁሟል። በብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ለመደራደርና በቀጣይም ብሔራዊ መግባባቱ ለማጠናከር ገለልተኛና ነፃ ተቋም ለመመስረት እንደሚያስችል ተገልጿል። በመሆኑም ኮሚቴው ለፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተሳትፎ ጥያቄ ማቅረቡና ተቀባይነት ማግኘቱን ኮሚቴው አመልክቷል። የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ ታዋቂ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተረጋጋች ሰላማዊትና ዲሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት በቅድመ ዝግጅት ሂደት የሃሳብ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል ኮሚቴው። ለጉባዔው ስኬታማነት መንግስት የበኩሉን እንዲወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠይቋል። በመጨረሻም ኮሚቴው የጉባኤውን ዓላማ ከመግለፅ ባሻገር የጉባኤውን ዝርዝር አንኳር ነጥቦችን ከመግለፅ ለመቆጠብ ወዷል። የአገር ውስጥ ኮሚቴው ከኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የሰማያዊ ፓርቲና የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላት ያሉበት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም