የመገናኛ ብዙሃን የአረንጓዴ አሻራን በተመለከተ የህብረተሰብ ንቅናቄ ፈጥረዋል--ብሮድካስት ባለስልጣን

75

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ( ኢዜአ) የመገናኛና ብዙሃን የአረንጓዴ አሻራን በተመለከተ የህብረተሰብ ንቅናቄ መፍጠራቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።

ኢታንግ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂዷል።  
 
በመርሃ ግብሩ ላይ አርቲስቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዱአለም እንዳሉት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ህብረተሰቡ በችግኝ ተከላ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ ነው።

 የአረንጓዴ አሻራ ስራ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ስራቸውን እንዲያጠናክሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

20 ቢሊዮን ችግኝ በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ለመትከል መዘጋጀት የይቻላል መንፈስ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡም በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የአረንገጓዴ አሻራ ዘመቻው ፍሬ ተጠቃሚ የሚሆኑ አገሮች ስራውን መደገፍ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ደግሞ አምባሳደር ቻም ኡጋላ ናቸው።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ አገሮች በደለል እንዳይቸገሩና ንጹህ ውሃ እንዲያገኙ የችግኝ ተከላውን ማገዝ አለባቸው።

አቶ ጎሳዬ ደበበ በበኩላቸው ''ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በችግኝ ተከላው ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል'' ብለው፤ የተከሉት ችግኝ እስኪጸድቅ እንክብካቤ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ ከተገኙት አርቲስቶች መካከል አንዱ የሆነው አርቲስት ሳምሶን ታደሰ ''ዛፍ መትከል ለህይወታችንና ለመጪው ትውልድ በመሆኑ ሁላችንም መረባረብ አለብን'' ብሏል።

በዚህ ዓመት የተቋቋመው ኢታንግ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የበጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ሀብተኢየሱስ ''ህብረተሰቡን በማስተባበር የአረንጓዴ አሻራ ለማሳረፍ መጥተናል'' ብለዋል።

በዚህ ዓመት ድርጅቱ 20 ሺህ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እንዳደረገም ጠቁመዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አሸብር አንበሴ በክፍለ ከተማው በዚህ ዓመት አንድ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ በራሱ ፍላጎት ችግኝ እየገዛ እየተከለ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ይፋ ከተደረገበት ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በክፍለ ከተማው 151 ሺህ ችግኝ ተተክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም